ዝክረ ሰሜን ዕዝ አንደኛ አመት

84

ዝክረ ሰሜን ዕዝ አንደኛ አመት-አንረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ

አሸባሪው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ያደረሰበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ሲዘከር ይኖራል።  አሸባሪው ህወሓት የሰሜን ዕዝን ድንገት አጥቅቶ የፈጸመው አስነዋሪ የሀገር ክህደት ወንጀል በኢትጵያ ታሪክ  ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል። ውሎ አዳራቸውን በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ አድርገው ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቁ የነበሩ የዕዙ የሠራዊት አባላት በራሳችን ወገን ያውም ጓድ እንዲህ ዓይነት ታሪክ የማይዘነጋው አስነዋሪና አሳፋር ድርጊት ይፈጸምብናል ብለው ፈጽሞ ባላሰቡትና በልገመቱት ሰዓትና ሁኔታ ከፊትና ከጀርባቸው ተወጉ።

ህልምና ስንቁ ሽብር የሆነው ህወሓት በእብሪትና በማን አለብኝነት ተነሳስቶ የፈጸመው ታሪክ ይቅር የማይለው ጥቃት እንዳሰበው ለኢትዮጵያ መፍረስና ለሕዝቦቿ መበታተን ምክንያት አልሆነም። ለሀገር ሉዓላዊነት ዘብ መቆም መገለጫቸው የሆነውና በታሪካቸው ሽንፈትን የማይቀበሉት ኢትጵያዊያን በእልህ፣ በቁጭትና በወኔ ከዳር ዳር ተነቃነቁ።

በመልካም ሥነምግባሩ የሚመሰገነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በራሱ ወገን የደረሰበት ጥቃት መሪርና ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም፤ የተቃጣባትን ጥቃት በእልህና በወኔ በመመከት ሀገርና ሕዝብን በማዳን የውስጥም የውጭም ጠላቶችን አንገት አስደፍቷል። ወገኑን ደጀን አድረጎ በሕግ ማስከበር ዘመቻው የተንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ  ሠራዊት የአሸባሪውን ህውሓት ሴራ በአጭር ጊዜ ውስጥ አከሸፈ። የአሸባሪውን ህውሓት ከፍተኛ አመራሮች ከፊሉን ደመሰሰ፣ ሌሎችን ከተደበቁበት ጎሬ አውጥቶ ለሕግ አቀረበ፤ የቀሩትን ተጠራርጎ በመደምሰስ አልያም  በቁጥጥር ስር በማዋል ደጀን ከሆነው ሕዝቡ ጋር በመሆን የሕልውና ዘመቻው አጠናክሮ ቀጥሏል።

አሸባሪው ህውሓት  ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰው ጥቃት ከትናንት በስትያ ''አንረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ'' በሚል መሪ ሀሳብ ታስቦ ውሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ዕለቱን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ነች። ልባም ልጆችዋ አጥር ሆነው የጋረዷት፣ ዋጋ ከፍለው ያደመቋት፣ ተቆጥሮ በማያልቅ መሥዋዕትነት ታፍራና ተከብራ የኖረች ሀገር ነች-ኢትዮጵያ።''ዛሬ የቆምነው ለእኛ ሲሉ የግፍ ጽዋን በተጎነጩ ጀግኖቻችን አጥንት ላይ ነው።''  ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአሸባሪው ህውሓት  ግፍ የተፈጸመባቸውን ጀግኖች ታሪክ ሲያስታውሳቸው ይኖራል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት  ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ አሸባሪውን ህውሓትን ሲፋለም ብዙ ዋጋ መክፈሉን፣ በየጦር ውሎው በጀግንነት እየተዋጋ ለውድ እናት ሀገሩ በመሰዋት ጭምር ለሀገርና ለወገን ያለውን አጋርነት በንግግር ሳይሆን በተግባር አሳይቷል። አሁንም ሀገርና ሕዝብን ለማዳን በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ይገኛል።

በኢትጵያ ታሪክ ውስጥ ሁሌም ሲታወስ የሚኖረውን የጥቅምት 24 መታሰቢያ በሀገሪቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ ውሏል። በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ዕለቱ ሲዘከር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እንዳሉት ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ በርካታ ኃይሎች በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ድል ተመተዋል። ''የምትፈርስ ሳይሆን በእኛ መሰዋዕትነት የምትቀጥል ጠንካራ ሀገር እንገነባለን።'' ይህን እውን ለማድረግ ኅብረተሰቡ ከሠራዊቱ ጎን መቆም አለበት። በተለይ ወጣቶች የመከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀል ሀገር የማዳን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዕለቱ ሲታሰብ ሀገር ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪውን ለመቅበር ቃል ኪዳን በመግባት መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ሰራተኞችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ዕለቱን ሻማ በማብራት ሥነሥርዓት አስበውት ውለዋል። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ባደረጉት ንግግር የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተዋቀረ የሀገር አንድነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱን ማጠናከር ኢትዮጵያን ማጠናከር ነው'፤ ለሠራዊቱ ክብር መስጠት ደግሞ የሀገር ወዳድነት ማሳያ ነው። የመከላከያ ሠራዊቱ ጥንካሬ የሚረጋገጠው በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተሳትፎ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ሠራዊቱን ከመደገፍም ባሻገር የሠራዊቱ አካል መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

እንዲሁም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም  ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመሆን አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ በግፍ የፈፀመውን ጭፍጨፋ "አልረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ ዕለቱ ታስቦ ውሏል። ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በሥነሥርዓቱ ላይ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት እኔ ያልመራኋት ሀገር ትፍረስ በሚል ክፉ መንፈስ መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውሶችን ሲፈጽም ቆይቷል። ከሁሉም የማይረሳው በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ክህደት ነው። አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በተባበረ ክንድ እየመከቱት ነው።ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ወታደር መሆናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል። ይህንኑ አጠናክረው ሀገርን የማዳንና ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ተልዕኳቸውን ከምንጊዜም በላይ ሊወጡ ይገባል።

ይህ ታሪካዊ ቀን በክልሎችም በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ ውሏል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ አስቸኳይ ጉባኤውን  የጀመረው  በአሸባሪው ህወሓት ሰሜን ዕዝ ላይ ለደረሰው  ጥቃት  የመታሰቢያ መርሃ ግብር አካሂዶ ነው። የምክር ቤቱ አባላት ለ45 ሰከንድ ቀኝ እጃቸውን በደረታቸው ላይ አድርገው፣ በግራ እጃቸው ጧፍ በማብራትና የኅሊና ፀሎት በማድረግ ዕለቱን አስበውታል። ዕለቱ በክልሉ በሚዛን አማን እና አርባ ምንጭ ከተሞችም ታስቦ ውሏል። በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የከተሞቹ ነዋሪዎች አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰው ጥቃት የውጭ ጠላት እንኳን ይፈጽመዋል ተብሎ የማይታሰብ ዘግናኝ ግፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ''የሽብር ቡድኑ እኩይ ድርጊት ኢትዮጵያዊነት በሰማዕታት መቃብር ላይ አብቦ እንዲያፈራ አድርጓል።'' በግፍ በተፈጸመው ድርጊት መላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥልቅ ሀዘን ቢሰማውም፤ ከጫፍ ጫፍ ተነቃንቆ በእልህና በወኔ በአንድነት በመቆም ለመከላከያ ሠራዊቱ ያለውን ደጀንነት በተግባር አረጋግጧል።

በኦሮሚያ ክልል የኢሉ አባቦራና የጅማ ዞን ነዋሪዎችም ዕለቱን በተመሳሳይ አስበው ውለዋል። የዞኖቹ ነዋሪዎች በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት የሰሜን ዕዝን ከጀርባ በመምታት የፈጸመው የሀገር ክህደት መቼም የማይረሳና ጥቁር ጠበሳ ጥሎ ያለፈ ታሪካዊ ክስተት ነው።አሸባሪው ህወሓት ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በማበር ሀገር የማፍራስ እኩይ ተልዕኮውን ለማሳካት በአማራና አፋር ክልሎች ንጹሃንን በግፍ ጭፍጭፏል፤ ንብረት ዘርፏል፤ አውድሟል፤ ሴቶችን በመድፈር ታሪክ ይቅር የማይለውን በደልና ግፍ ፈጽሟል፤ እየፈጸመም ነው። ሀገር ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪው ህወሓት ለመፋለም ዝግጁ ናቸው። ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ ዕለቱ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የጎንደርና የደባርቅ ከተሞች ነዋሪዎች ታስቦ ውሏል። ነዋሪዎች አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ክህደት ሀገር አፍራሽነቱን ያጋለጠ እኩይ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል። ጥቅምት 24ን ስናስብ  የአሸባሪው ህወሓት ግብዓተ መሬት በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ለማጠናቀቅ ቃል በመግባት ነው ብለዋል።

የአሸባሪውን ህወሓት እኩይ ተግባር ኢትዮጵያዊያን ላይ ቁጭት ፈጥሯል። ሕዝቡ ባሳየው የደጀንነት ተግባር የህግ ማስከበር ዘመቻው በተጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሠራዊታችን ራሱን አጠናክሮ ትግራይን ተቆጣጥሮ ለድል መብቃቱን ተናግረዋል።

ዕለቱን ደም በመለገስና በተለያየ ሥነሥርዓት አስበው የዋሉት የሐረር ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ግፍ የፈጠረባቸው ቁጭት የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር  የበለጠ አነሳስቷቸዋል።"በውጭ ኃይሎች እየተጋለበ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈራገጠውን ቡድን በፅናት ለመፋለም ዝግጁ ነን።" እንድ ጥንት አባቶቻችን ሀገርን ለማዳንና ከፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።

በጋምቤላ ከተማም ዕለቱ የክልሉ  ነዋሪዎችና ባለሥልጣናት በተገኙበት ታስቧል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት ለሃያ ዓመታት ሲጠብቀው በነበረው የሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ምንጊዜም በኢትዮጵያ ሕዝቦች ሲታሰብ ይኖራል። አሸባሪው ህወሓት የፈጸመው አስናወሪ ድርጊት ሰው በሆነ ፍጡር ሊደረግ ፈጽሞ የማይታሰብ አረመኔዊ ድርጊት ነው። የአሸባሪው ህወሓትና ተላላኪዎቹን ለመደምሰስ ለተጀመረው የሕልውና ዘመቻ ስኬት መላው የክልሉ ህዝብ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንዲወጣ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አአቅርበዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆረጦ የተነሳው አሸባሪው ህውሓት  ዛሬም እኩይ ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል። በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የበርካታ የንጹሃን ዜጎችን  ሕይወት ቀጥፏል። ዜጎች ጥረው ግረው ያፈሩትን ሀብት ንብረት የቻለው ዘርፏል፤ ያልቻለው አውድሟል።

ኢትዮጵያውያን አሸባሪውን ህወሓትና ተላላኪወቹን ዳግም የኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆኑ ለመደምሰስ ቆርጠው ተነስተዋል። የእናት ኢትዮጵያን ጥሪ ተቀብለው ከደጀንነት ድጋፍ ባሻገር የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን ተቀላቅለው አሸባሪው ህወሓትን መውጫ ቀዳዳ አሳጥተው ቁምስቅሉን እያሳዩት ነው። እውነት ምንጊዜም አሸናፊ ናት። የኢትዮጵያ የእውነት ፀሐይ እየወጣች ነው። ከራሳቸው ይልቅ ሀገርንና ወገንን በማስቀደም መስዋዕት በመሆን የዛሬዋን ቀን እንድናይ ያደረጉት በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባለት በዚህ የእውነት የፀሐይ ብርሃን ሁሌም ሲታወሱ ይኖራሉ። ድል ለኢትዮያና ለልጆቿ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም