ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውጤታማ አፈፃፀም የክልሉ ህዝብ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል

72

ጥቅምት 26 / 2014 (ኢዜአ) ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውጤታማ አፈፃፀም የክልሉ ህዝብ ድጋፍ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ ጥሪ አቀረበ።
የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አዱኛ አህመድ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነትና ከሕዝቡ የሚፈለገውን ትብብር አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በአዋጁ የተከለከሉ ተግባራትን በማስረዳት አዋጁ የወጣው በዋነኝነት የሕዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ካጋጠመው ችግር አንፃር በመደኛ የሕግ አካሄድ የአገር ሉዓላዊነትንና የሕዝብ ደህንነትን ማስጠበቅ ባለመቻሉ አዋጁ የወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

መንግስት የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሞራልና የሕግም ግዴታ እንዳለበትም ሊታወቅ ይገባል ነው ያሉት ወይዘሮ አዱኛ።

በአዋጁ ከተከለከሉ ተግባራት መካከል ከአሸባሪ ቡድኑን ሊያግዙ የሚችሉ ተግባራት፤ ማለትም ሓሳባቸውን ማሰራጨትና ሽብር መንዛት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የሽብር ቡድኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መደገፍ፣ በገንዘብም ይሁን በሌሎች መንገዶች ከቡድኑ ጋር መሆን የተከለከለ ተግባር መሆኑንም አንስተዋል።

በአዋጁ መሰረት ያልተፈቀደ ሰላማዊ ስልፍና ስብስባ ማድረግ የተከለከለ ሲሆን ማንነትን የሚገልጽ መታወቂያ መያዝም ግዴታ መሆኑን አስረድተዋል።

በአዋጁ የተደራጀው እዝ እንደ አሰፈካጊነቱ ትራንስፖርት ማገድ፣ መንገድ መዝጋት አመራሮችን ማገድ፣ መቀየርና መታካት እንደሚችል ጠቁመዋል።

በንግድ አሻጥር ውስጥ የሚሳተፉ የንግድ ማሕበረሰብ አባላትም ድርጊቱ ወንጀል መሆኑን በአዋጁ መስፈሩን አውቀው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

እነዚህን ክልከላዎች ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ ከሶስት ዓመት እስከ አስር ዓመት እስራት ያስቀጣዋል ነው ያሉት።

ከዚህም አልፎ የተፈጸመው ወንጀል ከፍተኛ ከሆነ በመደበኛ ሕጎች ጭምር ታይቶ ከእድሜ ልክ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ሊያስበይን ይችላል ብለዋል።

በሌላ በኩል አዋጁን ለማስፈጸም ከአቅም በላይ ሃይል መጠቀምና ያለ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋልም በአዋጁ መከልከሉን ተናግረዋል።

ሰላም በመንግስት ፍላጎትና ጥረት ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ መላው ሕዝብ ለአዋጁ ተፈጻሚነት ይተባበር ነው ያሉት።

በዚህም የክልሉ ሕዝብ የቤቱን፣ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም