ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነው የሕልውና አደጋ እስከወዲያኛው እንዲያከትም የስፖርት ማኅበረሰቡም ድርሻ ትልቅ ነው

81

ጥቅምት 26/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነው የሕልውና አደጋ እስከወዲያኛው እንዲያከትም በሚደረገው የሕዝብ ተሳትፎ የስፖርት ማኅበረሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከስፖርቱ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መክሯል።

በምክክሩ ወጣቶች፣ ፌዴሬሽኖችና የዘርፉ ባለድርሻዎች ለሕልውና ማስከበር ዘመቻው መሳካት የስፖርቱን ማኅበረሰብ ተሳትፎ አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል።

ምክትል የቢሮ ኃላፊው አቶ ጥበቡ በቀለ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሃሳብ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከፋፋይ ትርክቶቹን ቀጥሎበታል ብለዋል።

የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ለመነጠል አማራ ተነስቶብሃል፣ ኦሮሞ ተነስቶብሃል፣ አፋር ተነስቶሃል በሚል የማደናገሪያ ቅስቀሳ እየተጠቀመ እንደሆነም ተናግረዋል።

ይህም ሳይበቃው የውጭ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም በሚያሰራጨው ሀሰተኛ መረጃ ዓለምን እያሳሳተ ነው ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያ ላይ የደቀነው አደጋ እስከወዲያኛው እንዲያከትም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ የስፖርት ማኅበረሰብ ድርሻ ትልቅ እንደሆነም ጠቁመው።

የስፖርቱ ማኅበረሰብ የሽብር ቡድኑን ተላላኪዎች በማጋለጥ ለሕልውና ዘመቻው መሳካት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የስፖርት ማኅበሰቡ ግንባር ድረስ በመሄድ ጭምር ለመከላከያ ሠራዊቱና ለጸጥታ ኃይሉ ደጀንነቱን ማስመስከርና የተለያዩ ድጋፎችን ማጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

አሸባሪው ህወሓት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የሥነ-ልቦና ጦርነትም ከፍቷል ያሉት አቶ ጥበቡ ይህንንም መመከትና ትክክለኛውን መረጃ በመያዝ ራስን መጠበቅ ግድ ይላል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ጀይላን ሌንጂሶ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርሳቸው እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ የልዩነት መርዝ ረጭቶ ሄዷል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን ቡድን እስከ መጨረሻው ለማስወገድ ሁነኛ መድሃኒቱ አንድነት በመሆኑ በጋራ ቆመን ለሕልውና ዘመቻው ስኬት መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

መኖር የሚቻለው አገር ሠላም ስትሆን በመሆኑ በበኩሌ ለመዝመት ዝግጁ ነኝ ነው ያሉት።    

ወጣት ሱለይማን ሙደሲር ዜጎች በተለይም ወጣቶች በሕልውና ዘመቻው በንቃት እንዲሳተፉ ማነሳሳትና ማነቃቃት ያስፈልጋል፤ ለዚህም መገናኛ ብዙሃን በበቂ መጠን ሊሰሩ ይገባል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

አካባቢን ለመጠበቅ የሕዝቡና የፀጥታ ሃይሎች ቅንጅት ወሳኝ እንደሆነም ነው የተናገረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም