በክልሉ ከነገ ጀምሮ በግለሰቦች እጅ የሚገኝ የጦር መሳሪያ ምዝገባ ይካሄዳል

68

አሶሳ፤ ጥቅምት 26 / 2014 (ኢዜአ) በክልሉ ከጥቅምት 27/2014 ዓ.ም ጀምሮ በግለሰቦች እጅ የሚገኝ የጦር መሳሪያ ምዝገባ እንደሚካሄድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ  ሃላፊ አቶ መለሰ በየነ እንደገለጹት ምዝገባው ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት ይካሄዳል።

የአሸባሪውን ህወሃት ሀገር የማፍረስ ሴራ ህብረተሰቡ በተደራጀ አግባብ እንዲመክት ለማስቻል ምዝገባ ማካሄድ ማስፈለጉን አመልክተው፤ የክልሉ ነዋሪ በእጁ ላይ ያለውን የጦር ማሳሪያ በወቅቱ እንዲያስመዝገብ   ጥሪ አቅርበዋል።

የጦር መሣሪያ በእጃቸው እያለ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ቀርበው ምዝገባ ያላካሄዱ ግለሰቦች  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ ግብረሃይል በሚያደርገው ብርበራ ወቅት ቢገኝ ለመንግስት ገቢ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

አዋጁን መሰረት በማድረግ አሸባሪው  ህወሓት ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች የክልሉ ህዝብ የተለመደ አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የጦር መሳሪያ ምዝገባው የሚካሄደው በወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤቶች እና በየቀበሌው በሚገኙ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ ጽሕፈት ቤቶች እንደሆነ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም