በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትግበራ ወጣቱ የጎላ ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል

52

ጥቅምት 26/2014 (ኢዜአ)፡ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚነት ወጣቶች የጎላ ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ።
አስተያየት ሰጪዎቹ ወጣቶች የአዋጁ መደንገግ ብቻውን ግብ ባለመሆኑ ለተፈጻሚነቱ የወጣት ድርሻ ና ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በጎ ፈቃደኛና በተለያየ አደረጃጀት ያሉ ወጣቶች ለሠላም መስፈን ከጸጥታ አካላት ጋር በትብብር መስራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።      

ወጣት ናትናኤል ታምራት ያለንበት ሁኔታ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም ይላል።

በአዋጁ የተቀመጡ ክልከላዎችና የአፈጻጸም ሂደቱን መረጃ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ በማድረግ ክፍተቶችን ለመሙላት እንደ ወጣት የሚጠበቅብንን እንወጣለን ሲል ገልጿል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚፈለገው ውጤት እንዲያመጣ በማድረግ በኩል የወጣቱ ተሳትፎ ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም አክሏል።

ወጣቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማክበር ከራሱ ጀምሮ ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል ያለው ደግሞ  የወንድወሰን ሽፋ ነው።  

ወጣት ሃሊማ መሀመድም አገር ያለችበትን ሁኔታ በአግባቡ በመረዳት ወጣቱ ለሠላም መስራት አለበት ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም