አሸባሪውን ህወሓት ከምድረ ገጽ ካላጠፋን ኢትዮጵያ ሰላም አታገኝም-የአርባምንጭ ከተማ ወጣቶች

86

አርባ ምንጭ፤ ጥቅምት 26/2014 (ኢዜአ)፡ አሸባሪውን ህወሓት ከምድረ ገጽ ካላጠፋን ኢትዮጵያ ሰላም አታገኝም ሲሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች አስታወቁ፡፡

ወጣቶቹ የመንግስትን የክተት ጥሪን ተቀብለው በህልውና ዘመቻው በመቀላቀል የአሸባሪውን ህወሀት ወራሪ ሀይል ለመፋለም መዘጋጀታቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከከተማው ወጣቶች መካከል ወጣት ኢዮብ ምትኩ እንደገለጸው ''አሸባሪው ህወሓት በህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍ  የምንታገሰው ጉዳይ አይደለም ።

አሸባሪው ማሸነፍ እንደማይችል ሲረዳ  ያልተቆጣጠረውን ከተማ ተቆጣጥሬያለሁ፤ ያልማረከውን ሠራዊት ማርኬያለሁ፤ እያለ በተላላኪዎቹ አማካኝነት  በማህበራዊ ትስስር ገጽ የከፈተው ዘመቻ ህብረተሰቡን ሊያስደነግጥ እንደማይገባ ጠቁሟል።

''አሸባሪው ህወሓት  ከምድረ ገጽ ካልጠፋ  ኢትዮጵያ  ሰላም አታገኝም''  ያለው  ወጣት ኢዮብ የመንግስትን የክተት ጥሪ በመቀበል  ከመከላከያ  ሠራዊት ጎን  በመሆን ሽብርተኛውን ለመደምሰስ መዘጋጀቱን ተናግሯል።

የስልጣን ጥመኛው ህወሓት የትግራይ ወጣቶችን እያስጨፈጨፈ በመሆኑ የትግራይ ህዝብ  አሸባሪውን በማውገዝ  የበኩሉን ሊወጣ  እንደሚገባ  የጠቆመው  ደግሞ ወጣት  የሱነህ ሳሙኤል  ነው።

 ህወሀት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት ሳያንሰው በወረራ በያዛቸው የአፋርና የአማራ ክልል ንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለው ግፍና ሰቆቃ  ሰላምና  እንቅልፍ እንደነሳው አመልክቷል።

"ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እያሴረ ያለው ህወሓት ሙሉ ለሙሉ ካልጠፋ  ሀገር ሰላም አታገኝም "ያለው ወጣት የሱነህ  አካባቢውን በንቃት መጠበቅና ወደ ግንባር መዝመት  የወጣቱ ድርሻ በመሆኑ ዝግጁ መሆኑን ገልጻል።

አሸባሪው ህወሓት  ንጹሃን ዜጎችን  በማረድ፣ ደም  በማፍሰስ ፣  አስከሬን ላይ  በመጨፈርና  ሴቶችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመድፈር  በኢትዮጵያ ታሪክ ጥቁር አሻራ አስቀምጧል" ያለችው ደግሞ ወጣት ውሩ ካሳ ነች ።

አሸባሪውን ለመዋጋት ቆርጣ  መነሳቷን የገለጸችው  ወጣቷ በህብረተሰቡ  መካከል  ተቀላቅለው የሚያሴሩ ተላላኪዎችን በጥንቃቄ ማጥራት እንደሚገባ ጠቁማለች።

''በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሁላችንም  ከመንግስት   ጎን ከቆምን  ኢትዮጵያን  ማሻገር  አያቅተንም''  ያለችው ወጣት ውሩ " ለዚህም አንድነታችንን ማጠናከር አለብን" ብላለች።

"ወጣት ሙዘየን አብደላ በበኩሉ የውስጥና የውጭ ባንዳዎችን ለመመከት የበለጠ አንድ የምንሆንበት ሰዓት አሁን ነው" ብሏል።

ከአሁን ቀም የአንድ ወር ደመወዙን ለመከላከያ ሠራዊት መልቀቁን የገለጸው ወጣቱ  "እኛ ሌላ ሀገር የለንም፤ ለእዚች ሀገር ሰላም መከበር ስጋት የደቀነብንን  ጠላት  ለመመከት   ከመከላከያ  ሠራዊት ጎን በመቆምና መታገል አለብን "ብሏል።

ኢትዮጵያ ገናናነቷን ይዛ እንድትቀጥልና ሰላሟ እንዲረጋገጥ  የመንግስትን የክተት ጥሪ ተቀብሎ በህልውና ዘመቻው በመቀላቀል ህወሓትን ለመፋለም መዘጋጀቱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም