በግንባታ ላይ ካሉ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ልምድ እያገኘን ነው- ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች

72
አዲስ አበባ ነሀሴ 14/2010 በኢትዮጵያ በውጭ አገራት የስራ ተቋራጮች እየተገነቡ ካሉ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ልምድ እያገኘን ነው ሲሉ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ገለጹ። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ናቸው። የዚሁ አንድ አካል የሆነው በአፍሪካ የመጀመሪያው ረጲ የደረቅ ቆሻሻ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመርቆ አግልግሎት ጀምሯል። የፕሮጀክቱ ግንባታ በውጭ አገራት ስራ ተቋራጮች የተካሄደ ቢሆንም በዘርፉ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችም ተሳትፈውበታል። በመሆኑም ባለሙያዎች በአፍሪካና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የደረቅ ቆሻሻ የኤሌክትሪክ ሃይል ፕሮጀክት ልምድ መቅሰማቸውን ገልጸዋል። ባለሙያዎቹ የረጲ ደረቅ ቆሻሻ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከተጀመረ አንስቶ በዋናው ስራ ተቋራጭ ስር በባለሙያነት ማገልገላቸውን  ተናግረዋል። የረጲ ደረቅ ቆሻሻ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ባለሙያ የሆኑት ኢንጂነር ተወልደ ገብረሚካኤል  ፕሮጀክቱ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን አዲስ ብዙ ቴክኖሎጂ የያዘ  መሆኑን ተናግረዋል። በፕሮጀክቱ ላይ ከሚሰሩ የውጭ ባለሙያዎችበርካታ ልምድ ቀስመናል ብለዋል፡፡ ሌላው ኢንጂነር ጎሹ ንጉሴ በበኩላቸው ሲቪል መሃንዲስ እንደሆኑና  ብዙ ነገሮች ኮንትራክተሮች ጋር እና ከብዙ ሰብ ኮንትራክተሮች ጋር በመስራት ብዙ ሙያ አግኝቼበታለሁ ብለዋል፡፡ በዚህም ከፍተኛ የሚባል ልምድ ከውጭ አገራት ባለሙያዎች ማግኘት ችለናል ነው ያሉት። ይህም አገሪቱ የጀመረችውን የሃይል ማመንጨት እንቅስቃሴ በተሳካ ሁኔታ እንድታከናውን ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ነው ባለሙያዎች ያስረዱት። በሌላ በኩል ሌሎች የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግንባታዎችን በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ሙሉ አቅም ለመስራት እንደሚያግዝ ተናግረዋል። የረጲ ደረቅ ቆሻሻን የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ በዋና የስራ ተቋራጭነት ያከናወነው ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ዘነበ በግንባታው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል። ይህም አገሪቱ የጀመረችውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው ሽግግር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል። ግንባታውን ባከናወነው በካምብሪጅ ስራ ተቋራጭ ውስጥም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ልምድ ማግኘታቸውን ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ባለሙያዎቹ በሚያገኙት ልምድ ከአገር አልፈው በሌሎች የአፍሪካ አገራት በሚገነቡ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ስራዎች ላይ የመሳተፍ ዕድል እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም