በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ሥራ ጀመረ

52

አሶሳ ጥቅምት 26 /2014 (ኢዜአ)  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩ ተገለጸ፡፡
የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለሰ በየነ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ትናንት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ የሥራ ዕቅዱን አዘጋጅቶ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡

ዕዙ ተጠሪነቱ ለርዕሰ መስተዳድሩ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው በእዙ ውስጥ የሀገር መከላከያ፣ የክልሉ እና የፌደራል ፖሊስ፣ የሠላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ፣ የብሔራዊ ደህንነት እና ሌሎችም በአባልነት መካተታቸውን አመልክተዋል፡፡

የእዙ ዋነኛ ዓላማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በአግባቡ ማስፈጽም መሆኑን አመልክተዋል።

አቶ መለሰ እንዳሉት መምሪያ እዙ በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ የአስቸካይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽሙ ግብረሀይሎችን ያቋቁማል።

በክልል ደረጃ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ጋር በተገናኘ ያሉ የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ሥራዎችን የማስተባበርና የመከታተል ተግባርም ያከናውናል።

"ከእዚህ በተጨማሪ በክልል ደረጃ የአዋጁን ዓላማ ለማሳካት የሚሰሩ የህዝብ አደረጃጀት እና እንቅስቃሴ ስራዎችን ያስተባብራል፤ ይከታተላል" ብለዋል።

አቶ መለሰ እንዳሉት ከአዋጁ ጋር በተገናኘ የሚኖሩ የህዝብ ቅሬታዎች ምላሽ እንዲያገኙ ከሚያደርገው ክትትልና ድጋፍ በተጨማሪ በክልል ደረጃ በሽብርተኛው ቡድን የተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ተገቢ ድጋፍ እንዲያገኙ እዙ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።

ከፌደራል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ የጸጥታ ኮሚቴ ጋር በተናበበ መንገድ በክልሉ የጸጥታ ማስከበር ሥራዎችን የመምራትና የማስተባበር ሥራዎችን እንደሚያከናውን አቶ መለሰ አስታውቀዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም