አሸባሪው ህወሃት የከፈተብንን ጦርነት ለመቀልበስ እንዘምታለን

80

ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 26/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን የከፈተውን ጦርነት በመቀልበስ ኢትዮጵያን በማዳኑ ዘመቻ ለመሳተፍ ወደ ግንባር እንደሚዘምቱ የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች አስታወቁ።

አሸባሪው ኢትዮጵያን እኔ ካልመራሁ አትኖርም በሚል እብሪት ሀገር ለማፍረስ ቢፍጨረጨርም  እንደማይሳካለት ወጣቶቹ በክልሉና በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጋምቤላ ከተማ በተወያዩበት ወቅት ገልጸዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት አሳምነው ተፈሪ፤ አሸባሪው ህወሓት ግብረአበሮቹን ከወጭ ጭምር በማምጣት ሀገር ለማፍረስ ሌት ተቀን እየሰራ  መሆኑን ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያን እኔ ካልመራሁ አትኖርም በሚል ሀገር ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስና ሀገር ለማዳን የማንዘምትበት ምክንያት አይኖርም’’ ብሏል።

በተጨማሪም ከጉያችን ስር ሆነው ለአሸባሪው  ቡድን የሚላላኩ ቅጥረኞችን ጭምር አጋልጦ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ያመለከተው  ወጣት አሳምነው፤ መንግስት የህዝብን ጥቆማ በመቀበል ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

ለሀገር ዘምቶ መሞት አኩሪ ታሪክ በመሆኑ የአሸባሪዎችን ሀገር የማፈረስ ሴራ ለመቀልባስ ወደግንባር እንደምትዘምት ያስታወቀችው  ደግሞ ወጣት አባንግ ኮመዳን ናት።

በክልሉ እየተስፋፋ ያለው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለአሸባሪዎቹ ተላላኪዎች እኩይ ተግባር ማስፈፀሚያ ሊውል ስለሚችል ችግሩን ለመግታት መንግስት ጠንክሮ እንዲሰራ ጠይቃለች።

ወጣት ተስፋዬ ድልነሳ በበኩሉ፤ የክልሉ ወጣት ባለፉት ሦስት ዓመታት ያገኘውን ሰላም በማንም የሽብር ቡድን ዳግም ማጣት አይፈልግም ብሏል።

"አሸባሪው ህወሓት ሀገር ለመበተንና ንጹሀንን ለመጨፍጨፍ ሌት ተቅን እየሰራ እኔ ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት መስዋዕት የማልሆነበት ምክንያት የለም"

ቀደም ሲል የክልሉን ሰላም ሲነሳ የነበረውን የአሸባሪው ህወሓት ቡድንን በግንባር ለመፋለም እሱን ጨምሮ ወጣቱ ለመዝመት መነሳሳቱን ተናግሯል።

የጋምቤላ ክልል  ወጣቶች ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት አችዎድ ባች "በቅጥረኛ የሽብር ቡድን የጥፋት ተልዕኮ ኢትዮጵያ ስትፈርስ ወጣቱ ዝም ብሎ አይመለከትም" ብሏል።

በሀገር ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስና ሰላምን ለማረጋገጥ ወጣቱ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመሰለፍ ክልሉን ብሎም ሀገሪቱን ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጧል።

"አሸባሪውን ህወሓትና ግብረአበሮቹን የመፋለሙ ሂደት ለሀገር መከላከያና ለሌሎች የጸጥታ አካላት ብቻ መተው አይገባም" ያለው ደግሞ የክልሉ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ሯች ጉዊች ነው።

ቡድኑ በሀገር ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በተለይ የክልሉ ወጣት ግንባር ቀደም በመሆን ሊዘምት እንደሚገባ ተናግሯል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጀት፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገር የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ የክልሉ ነዋሪዎች በዘርና ፆታ ሳይገደቡ የህልውና ዘመቻውን ሊቀላቀሉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በውይይት መድረኩ የወጣቶች ሊግ እና ፌዴሬሽን አባላት ጨምሮ የጋምቤላ ከተማ ወጣት ተወካዮች ተሳታፊ ሁነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም