የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለው ያልተገባ ጫና ሊያበቃ ይገባል- የጅማ ነዋሪዎች

51

ጅማ፣ ጥቅምት 26/ 2014 (ኢዜአ) የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለው ያልተገባ ጫና ሊያበቃ ይገባል ሲሉ የጅማ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ጠየቁ።

ነዋሪዎቹ ዛሬ ባካሄዱት ህዝባዊ ሰልፍ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ የውጭ ሀይሎች ጫናንን በማውገዝ አሸባሪዎችን ህወሀትና ሸኔን ለመደምሰስ እየተካሄደ ላለው የህልውና ዘመቻ ድጋፋቸውን ገልጸዋል ።

ነዋሪዎቹ አሸባሪዎቹ ህወሀትና ሸኔ የከፈቱትን ጦርነት በመመከት ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ነዚፋ ሁሴን  እንዳለችው አሸባሪው ህወሀት ሀገር ለማፍረስ የያዘውን ሴራ ለማሳካት በከፈተው ጦርነት ንጹሀንን በመጨፍጨፍ፣ ንብረት በመዝረፍና በማውደም እንዲሁም ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር እየፈጸመ ያለውን ግፍ ቀጥሎበታል።

ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ የውጭ ሀይሎች እውነታውን ወደ ጎን በመተው መንግስትና ህዝብ ወራሪውን ለመመከት እያካሄዱት ባለው የህልወና ዘመቻ አሸባሪው ሽንፈት ሲደርስበት እየጠበቁ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን እያደረጉ መሆናቸውን ገልጻለች።

በውጭ ሀይሎች ጫና የሚንበረከክ ኢትዮጵያዊ አለመኖሩን የገለጸችው ወጣት ነዚፋ ማንኛውም የውጭ ሀይል በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት በሉአላዊት ሀገር ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር የሚያደርገውን ሙከራ ሊያቆም እንደሚገባ አመልክታለች።

"የታሪካዊ ጠላቶቻችን ተላላኪ የሆኑ አሸባሪ ህወሀትና ሸኔን በመመከት የሀገርን ሉአላዊነትን ለማስከበር በየትኛውም ጊዜ ለመነሳት ዝግጁ ነኝ" ብላለች።

አቶ ጋሮምሳ ገመቹ በበኩላቸው "የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ እያሳደሩ ያለው አይን ያወጣ ጫና ሊበቃ ይገባል" ብለዋል።

"ሁላችንም ዘምተን የሀገርና የህዝብ ጠላት የሆነውን ክፉ መዥገርህ ማጥፉት አለብን" ብለዋል።

"በግንባር ተሰልፈን በመፋለም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያለንን ድጋፍ ማሳየት አለብን " ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል።

የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ የውጭ ሀይሎች ጫናን የምትሸከም ሀገር ሳትሆን ወራሪዎችን ድል በመንሳት ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት የሆነች ሉአላዊት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

የውጭ ሀይሎች ለአሸባሪ ህወሀት በመወገን በሀገር ላይ ጫና ለማሳደር የሚያደርጉትን ሙከራ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

"የሽብር ቡድኖቹ ያደረሱብንን መከራና ውድመት ታሪክ የማይዘነጋው ሆኖ እያለ የበደሉን አልበቃ ብሏቸው ዛሬም ንጹሀን እናቶችና ህጻናትን እየገደሉ ነው" ብለዋል።

"ከሀገር ህልዉና የሚበልጥ ምንም ነገር ስለሌለ ሁላችንም ለሀገራችን የመጨራሻውን መስዋእትነት ለመክፈል በመዘጋጀት ለሀገራዊ ጥሪዉ መነሳት አለብን " ብለዋል።

"ማንኛዉም ለትግል ብቁ የሆነ ግለሰብ የህልውና ዘመቻውን ለመቀላቀል ከዛሬ ጀምሮ ይዘጋጅ" ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ነጁብ አባራያ " ህዝባችንን በመከፋፋል የጥላቻ ዘሩን ሲዘራ የኖረው አሸባሪው ቡድን የኦሮሞን ህዝብ ዘርፏል፣ አፈናቅሏል ዛሬም ቀጥሎበታል" ብለዋል።

"ግፈኛና አረመኔ ህወሀትን እስከ ተላላኪው ሸኔ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ከምድረ ገጽ ልናጠፋቸው ይገባል" ሲሉ ከንቲባው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም