ሪፖርቱ የአሸባሪውን የውሸት ጦር ሰፈር ያፈረሰ ነው

98

አሸባሪው ህወሃት በጦር ግንባር ፊት ለፊት ከመግጠም በላይ በሐሰት ፕሮፓጋንዳ የሚያካሂደው ዘመቻ ከፍ ያለ መሆኑ ይታወቃል።

ለዚህ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻው የሚሆን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ማካሄጃ ጦር ሰፈር በማደራጀት ረገድ የተካነ ነው። ቡድኑ ኢትዮጵያን በገዛበት ዘመነ ስልጣኑ ለፕሮፓጋንዳው የሚሆን ዝግጅት ሲያደርግ መኖሩ የአደባባይ ምስጢር ነው።

የስልጣን አጋጣሚውን በመጠቀም ቆርጠው የሚቀጥሉ ነጩን ውሸት እውነት አስመስለው የሚያቀርቡለትን ሰዎች አቅም በመገንባት ጊዜውን አሳልፏል።አሸባሪው ቡድን በፕሮፓጋንዳ አገልጋይነት ያሰለጠናቸው ሰዎች ዛሬ በውሸት አገር ለማፍረስ ዘመቻ ውስጥ የገቡት።

ቡድኑ ከመንግስት ካዝና በጀት መድቦ የውሸት ዘመቻ ማካሄጃ የጦር ሰፈር ከመገንባት በላይ ደግሞ የእሱ ተከፋይ የሆኑ የውጭ መገናኛ ብዙሃን፣ ተቋማትና ግለሰቦች የቡድኑን ውሸት በማግነንና የኢትዮጵያን እውነት በመድፈቅ በርካታ ለአገር ስጋት የሚሆን ተግባር ፈጽመዋል፤ አስፈጽመዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የውሸት ፕሮፓጋንዳው ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርሱ ምቹ መደላድል ፈጥሮላቸዋል።ነገር ግን አበው ‘እውነት ትቀጥናለች እንጅ አትበጠሰም’ እንዲሉ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የተደፈቀው የኢትዮጵያ እውነት በመጠኑም ቢሆን ቀና የሚልበት ዕድል በዚህ ሳምንት ታይቷል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የጋራ የምርመራ ቡድን የቀረበው የምርመራ ውጤት ሪፖርት የአሸባሪውን የውሸት ጦር ሰፈር የማፍረስ ጅማሬ ሆኗል።

የአሸባሪው ህወሓት የውሸት ፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ የሆነው የውሸት ጦር ሰፈር በተቋማቱ የጋራ የምርመራ ሪፖርት አማካኝነት የመፍረስ ጅምር ላይ ይገኛል። ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል በሚል ብሒል የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ይቀርቡ የነበሩ ውንጀላዎችን የሚደግፍ ማስረጃ ያለመኖሩን ሪፖርቱ አረጋግጧል።

በተለይም መንግስት ረሃብን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ነው፤ የሰብዓዊ ድጋፍ ሂደትን እያደናቀፈ ነው፤ በሴቶች ላይ አስገድዶ የመድፈር ወንጀል እየተፈጸመ እንደሆነ አጋንኖ በመግለጽ የኢትዮጵያ መንግስት ጫና ውስጥ እንዲገባ ሲደረግ ቆይቷል። የሪፖርቱ መውጣት ግን የአሸባሪው ህወሃት የውሸት ፕሮፓጋንዳ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ በመቸለስ ውንጀላውን የሐሰት መሆኑን ለዓለም ለማሳየት ሞክሯል።

አሸባሪው ህወሃት ስልጣን ላይ በቆየበት 27 አመት በፈጠረው አለም አቀፍ መረብ በመጠቀም ከፍተኛ የሃሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ከአለም አቀፍ ማህበረሰቡን ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ከስልጣን በህዝባዊ እምቢተኝነት ከተባረረም በኋላ ዲጅታል ወያኔ የተባለ ቡድን በማቋቋም ከፍተኛ የውሸት መረጃ በማሰራጭት ስራ ላይ ተጠምዶ ይገኛል፡፡

በሚያሰራጨው የውሸት፣ የተሳሳተና የተዛባ መረጃ አማካኝነት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ለማዋረድ ሞክሯል፤ የአገርን ሉአላዊነትን አስደፍሯል፤ በንጹሃን ላይ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አድርሷል፤ በእናት አገሩ ላይ ክህደት ፈጸሟል፤ ከባዕዳን ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ወግቷል፤ እየወጋም ይገኛል፡፡ ከውሸት የጦር መንደሩ የሚያሰራጨው መረጃ አላማም አገር በማፈረስ የባዕዳንን ጥቅም በማስጠበቅ ወደ ሞግዚትነት የስልጣን መንበሩ ለመመለስ ነው፡፡ ቡድኑ አገር የመበትን ሴራውን ለማሳካት የሚታወቅበት እኩይ የሴራ ተግባሩ ረጅም እርቀት ያስጓዘው መስሎ ታይቷል፡፡

በተለይም ከውሽት የጦር መንደሩ የኢትዮጵያ መንግስት እረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ነው፣ ትግራይ ከበባ ውስጥ ናት፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ማደናቀፍ፣ የአለም አቀፍ ተራድዕ ድርጅቶችና ጋዜጠኞችን ወደ ትግራይ እንድይገቡ ማገድ፣ ትግራይ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተቋርጦባታል፣ የዘር የማጥፋት ወንጀል በትግራይ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ነው የሚሉ የውሸት መረጃዎችን በአለም አቀፍ መረቡ ተጠቅሞ ሲያስራጭ ቆይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በማኅበራዊ ሚድያ ገጻቸው ላይ ባወጡት ጽህፍ "ሲቀርቡብን የነበሩ ወቀሳዎች በእኛ በኩል ሐሰት መሆናቸውን ብናውቅም ጠላቶቻችን ግን ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ሲያታልሉት ቆይተዋል" ብለዋል።

ነገር ግን እነዚህ የሐሰት መረጃዎች እንደ እውነት ተቆጥረው በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መነገራቸውና ተቀባይነት ሲያገኙ መቆየታቸው አስገራሚ ነው ሲሉም አክለዋል።

ሪፖርቱ እንደሚጠቁመው ህወሓት ግጭቱን ከመጫር አልፎ እጅግ ሰቅጣጭ የሆኑ በደሎችን የፈጸመ መሆኑን ነው። ነገር ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን አይቶ እንዳላየ አልፏልም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ _ አካባቢህን ጠብቅ _ ወደ ግንባር ዝመት _ መከላከያን ደግፍ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም