ኢሶዴፓ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ የጂግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

62
ጂግጂጋ ነሀሴ 13/2010 የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጂግጅጋ ከተማ  ነዋሪዎች ገለጹ። ፓርቲው በቀጣይ ተከስቶ በነበረው ሁከት እጃቸው ያለበትን አመራሮች ለህግ ማቅረብ እንዳለበትም አክለዋል። በሶማሌ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት የሰው ህይወትን ጨምሮ በመንግስትና በግለሰብ ንብረቶች ላይ ጉዳት ደርሷል። ሁነቱን ተከትሎ ኢሶዴፓ  በካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ አቶ አህመድ ሽዴን የፓርቲው ሊቀመንበር  አድርጎ መሾሙ ይታወቃል። የፓርቲው ሊቀመንበር አህመድ ሽዴ ትናንት በሰጡት መግለጫ መሰረት የፓርቲው አመራሮች የእርስ በርስ ግምገማ ካደረጉ በኋላ ሶስት የፓርቲው ማዕከላዊ አባላትንና አምስት ስራ አስፈጻሚዎች እንዲታገዱ ተወስኗል። በቀጣይም ከጎሳ መሪዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማገሌዎች ጋር በመነጋገር አዲስ የአመራር መዋቅር እንደሚፈጠርም አቶ አህመድ ሽዴ አክለዋል። ይህን ውሳኔ በማስመልከት ኢዜአ በጂግጅጋ ተገኝቶ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ፓርቲው እየወሰደ ያለውን እርምጃ ደግፈዋል። አቶ መሃመድ አብደላ ፓርቲው የወሰደው እርምጃ ትክክል መሆኑን ገልጸው፤ በህገ ወጥ ድርጊት የተሳተፉ አካላትን ከማገድ በዘለለ ለህግ ማቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል። በፓርቲው ውሳኔ መደሰቱንና በቀጣይ የክሌሉን ህዝብ  የሚወድ አመራር ወደ ኃላፊነት መምጣት እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ አቶ አሪፍ በዱል ናቸው። ''በጣም ደስ ብሎናል። ያጋጠመንና ያሳለፍነው ችግርና ስቃይ ላይ የተሳተፉትን በማገዳቸው ተደስተናል። የነበረው አመራር ከታች እስከ ላይ ተነስተው አዲስ አደረጃጀት አገሩንና ህዝቡን የሚወድ መንግስት የተማሩና ጭንቅላት ያላቸውና ለአገሪቱ  እና ለህዘቡ የሚያዝኑ ሰዎች መምጣት አለባቸው'' ብለዋል። አቶ ፉአድ ሃሰን በበኩላቸው በክልሉ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ዝርፊያ ላይ የአመራሩ እጅ እንዳለበት በተደጋጋሚ ይነገር እንደነበር አስታውሰው፤ ፓርቲው በከፍተኛ አመራር ደረጃ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ የሚደገፍ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። ከጉዳቱ መጠን አንጻር አሁንም መጠየቅ የሚገባቸው አመራር መኖር እንዳለባቸው የገለጹት አቶ ፉአድ፤ የፓርቲው አመራር በፍጥነት ከክልሉ ህዝብ ጋር ውይይት እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ''መደበኛ ጉባኤውን በፍጥነት ማካሄድ አለበት በየደረጃው ያሉትን መርጦ በአዲስ የተማረ ሃይል ማዋቀር አለበት'' በማለት ገልጸው የለውጥ እርምጃው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም