የሲቲ ዞን ነዋሪዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ለማቋቋም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገለጹ

55
ድሬደዋ13/2010 በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን  የአይሻ እና የሽንሌ አካባቢ ነዋሪዎች በጅግጅጋና ሌሎች ከተሞች  የተፈናቀሉ ወገኖችን  ለማቋቋም መንግስት  የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገለጹ፡፡ የኃይማኖት አባቶችና ወጣቶች ጨምሮ  በአይሻ እና ሽንሌ አካባቢ የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተብ ክፍሎች በወቅታዊ ጉዳይና ተፈናቃዮችን መርዳት በሚችሉበት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡ በዚህ ወቅት ነዋሪዎቹ በጂግጅጋና ሌሎች ከተሞች ተፈጥሮ በነበረው ሁከት በሰውና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው ለተጎጂዎቹ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡ በውይይቱ ከተሳተፉት ነዋሪዎች መካከል የ80 ዓመቱ አዛውንት አቶ መሐመድ መሐሙድ በጅግጅጋና ሌሎች የሶማሌ ከተሞች በዜጎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡ " ድርጊቱ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በፍቅር የሚኖረውን የሶማሌ ህዝብ አይወክልም "ብለዋል፡፡ መንግስት እነዚህን አካላት በአፋጣኝ ለመያዝ ለህግ በማቅረብ  ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙና ተጎጂዎችንም መካስ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚደረገው  ጥረት በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ "እህት ወንድሞቻችንን ለማቋቋም በሚደረገው ማንኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል" ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ሐቦን ሐሰን ናቸው ፡፡ አቶ ሱሌይማን በሸር በበኩላቸው በክልሉ በዜጎች ላይ የተፈፀመው ኢሰብአዊ ድርጊት አውግዘው "ህዝቡ በተረጋጋ መንፈስ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ተቀናጅቶ ለሀገር ሰላምና ፀጥታ ጠንክሮ መስራት ይገባዋል" ብለዋል፡፡ ተፈናቃዮችን  ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እንዲመለሱ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ ወይዘሮ ማሃዶ ሙስጠፋ ናቸው፡፡ "  እኛም ከመንግስት ጎን በመሆን የዜግነት ኃላፊነታችን እንወጣለን" ብለዋል፡፡ ከ20 ዓመት በላይ በአይሻ ወረዳ እንደኖሩ የተናገሩት  ሻምበል ተክላይ አፅበሃ በበኩላቸው  በከተማዋ ሁሉም ብሔሮች በፍቅርና  በአንድነት የሚኖሩ፣ በሀዘንና በደስታ የማይለያዩ ጠንካራ ህብረት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ልክ በጅግጅጋ የተፈጠረውን ኢሰብአዊ ድርጊት በማግስቱ በአይሻ ለመድገም የተደረገው ቅስቀሳና ሙከራ በሶማሌ ወንድምና እህቶቻቸው ደጀንና አይበገሬነት ሣይሳካ መቅረቱን አመልክተዋል፡፡ የተፈናቀሉ  ወገኖችን ለማቋቋም   የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸው  አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ውይይቱ  በሲቲ ዞን በሚገኙ ሌሎች ወረዳዎችም እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም