ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰሩትን የውስጥና የውጭ ጠላቶች በጋራ ለመመከት ቁርጠኞች ነን

116

አዲስ አበባ ጥቅምት 25/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰሩትን የውስጥና የውጭ ጠላቶች በጋራ ለመመከት ቁርጠኞች ነን ሲሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ በልጆቿና ታፍራና ተከብራ የኖረች አገር መሆኗ እሙን ነው።

ታዲያ ይህችን ታላቅ አገር አሸባሪው ህወሓት ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ለማፍረስና ታሪኳን ለማንኳሰስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ማንነቷንና ታሪኳን አሳልፈው የማይሰጡ በመሆናቸው እነዚህን ኃይሎች ለመመከት በአንድነት ተነስተዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰሩ ኃይሎችን በተባበረ ክንድ የምንመክትበት ጊዜ አሁን ነው ይላሉ።

በተለይም የውጭ ኃይሎች በአገሪቷ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ ያስቻላቸው የውስጥ ጠላቶች ድጋፍ መሆኑን በማንሳት ይህንን በጋራ መታገል ይገባል ብለዋል።

የውጭ ጣልቃ ገቦች በጦርነቱ ጭምር በመሳተፋቸው "አዝኛለሁ" ያሉት አቶ አድማሱ አቄኔ በበኩላቸው ሕዝቡ ጠላቶቹን ለመመከት ከምንግዜውም በላይ በጋራ መቆም አለበት ብለዋል።

አቶ መሃሪ ፋንታሁን፤ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ እንዲባባስ ያደረጉት የውጭ ኃይሎች መሆናቸውን ገልጸው ይህን ጣልቃ ገብነት ለመመከት በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል።

ጠላትን ከመመከቱ ተግባር ጎን ለጎን የተጀመሩ የልማት ሥራዎችንም ማስቀጠል የሚገባ መሆኑን ጠቅሰው ለዚሀም ሁሉም ያለውን  እውቅት፣ ገንዘብና ጉልበት በመጠቀም ሊንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።

ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን የሚያወጣቸውን ሕግና መመሪያዎች መተግበር እንደሚኖርበት ገልጸው፤ እነዚህን ተግባራት ለመፈጸም ግንባር ቀደም እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል።

ሠላም ለአንድ አገር ሕዝብ የህልውና መሰረት በመሆኑ ሁሉም ለሠላሙ ቅድሚያ ሰጥቶ በመሥራት የውስጥ ጉዳዮችን በውስጥ መጨረስ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ  አቶ ነብዩ ብርሃኑ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም