በአዲስ አበባ የችግረኛ ተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም የበጀት እጥረት እየፈተነው እንደሆነ ተገለጸ

42
አዲስ አበባ ነሃሴ 13/2010 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የመንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ችግረኛ ተማሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት የምገባ ፕሮግራም የበጀት እጥረት እንዳጋጠመው ተገለጸ። በየትምህርት ቤቶቹ ችግረኛ ተማሪዎችን የምገባ ፕሮግራም የሚያከናውነው የእናት ወግ በጎ አድራጎት እንዳስታወቀው ፤ የበጀት እጥረት ፈተና ሆኖበታል፡፡ የበጎ አድራጎቱ ስራ ዋና አስኪያጅ ወይዘሮ ደብረወርቅ ሉልሰገድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በ2009 ዓ.ም መጨረሻ ችግረኛ ተማሪዎችን ለመመገብ የሚያስችል በጀት ከተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም በጥቅሉ ወደ 70 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ቃል ቢገባም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆን ገንዘብ ለድርጅቱ ገቢ መሆን አልቻለም። ማሰባሰብ የተቻለው 30 ሚሊዮን ብር ያህል እንደሆነ ጠቁመዋል። በተለይም 10ሺህ ተማሪዎችን በየአመቱ የሚመግበው ሚድሮክ ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ቃል በገባው ልክ ድጋፍ ባለማድረጉ የበጀት እጥረት ሊያጋጥም መቻሉን ዋና ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል፡፡ በዚህም በ2010 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተጨማሪ ተማሪዎችን የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለማድረግ የታሰበ ቢሆንም በበጀት እጥረትና በዋጋ ንረት የተነሳ ተግባራዊ ማድረግ እንዳልተቻለ ወይዘሮ ደብረወርቅ ይናገራሉ፡፡ የበጀት ችግሩ ምገባውን እንዳያቋርጠው በማሰብ ነባር ተመጋቢዎችን ብቻ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ ብቻ ሊከናወን መቻሉን ጠቁመዋል። ቃል የተገባውን ያህል ሀብት መሰብሰብ ባይቻልም በ2010 የትምህርት ዘመን ለ22 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች ምገባ መካሄዱን ዋና ስራ አስኪያጇ ገልጸዋል፡፡ ለ2011ዓ.ም የትምህርት ዘመንም በቅርቡ ሀብት የማሰባሰብ ስራ እንደሚከናወን የጠቆሙት ወይዘሮ ደብርወርቅ ለምገባ ፕሮግሙ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ለችግረኛ ተማሪዎቹ ምገባ ፕሮግራም ሁሉም ወገን የሚችለውን ያህል ድጋፍ እንዲያደርግ ወይዘሮ ደብርወርቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በአዲስ አበባ የችግረኛ ተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በ2007 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በእናት ወግ በጎ አድራጎት ከ22ሺህ እንዲሁም በተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከ10ሺህ በላይ የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም