እየተዋጋን ያለነው በነውራቸው ከሰከሩ ጋር ነው

69

ጥቅምት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) “እየተዋጋን ያለነው በነውራቸው ከሰከሩ ጋር ነው” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሃት በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ተካሂዷል።

በመርሀ ግብሩ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የመከላከያ የሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ከንቲባዋ መርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው የህወሀት ቡድን አረመኔያዊ የክህደት ተግባር በወገኑ ላይ ፈጽሟል። ህይወቱን ሁሉ ለህዝብ ሰጥቶ የኖረ ጀግና ሰራዊትን ከኋላው በማጥቃት አሸባሪው ቡድን የክህደቱን ጥግ ማሳየቱን አስታውሰው፤ “እየተዋጋን ያለነው ከእንደዚህ አይነት በነውራቸው ከሰከሩ ጋር ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

“የአሸባሪውን ቡድን ማንነት ህብረተሰቡ በደንብ ያውቀዋል” ያሉት ከንቲባዋ፤ አሸባሪው ቡድን በሐሰተኛ ወሬና ፕሮፓጋንዳ ህዝብ ለማጭበርበር እየጣረ መሆኑን አመላክተዋል። አሁንም ቢሆን በውክልና ጦርነት ባእዳን እየጋለቧቸው ታሪክ ለማበላሸት እየጣሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደት የፈጸመውን አሸባሪና ከሀዲ ቡድን በአንድነትና በትብብር በመደምሰስ የቀደምት አባቶችን ታሪክ መድገም እንደሚገባ ገልጸዋል። የመከላከያ የሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ በበኩላቸው አሸባሪው ቡድን አፈ ቀላጤዎቹ አማካኝነት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንደሚሰራ ማረጋገጡን ተናግረዋል።

‘ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እሰራለው’ ማለቱን አስታውሰዋል። “ኢትዮጵያውያን በድንጋይ ያባረሩት ቡድን ዛሬ ላይ መሳሪያ ይዞ ዳግም ካልጨቆንኳችሁ እያለ ነው” ሲሉም አክለዋል።

“ድል እንደምናደርግ ቅንጣት ጥርጥር የለንም” በማለት ገልጸው፤ አሁንም ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አመልክተዋል።

“አሸባሪው ቡድን እና ጋላቢዎቹ እንዲሁም የኛን ባርነት የሚመኙ ጭምር በተባበረ ክንድ ይመለሳል” ሲሉም ገልጸዋል። በመርሀ ግብሩ በሰሜን እዝ ጥቃት ለተሰዉ የሰራዊቱ አባላት የህሊና ጸሎት ተደርጓል።

"ሻማችን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ ለተሰውት መከላከያ ሰራዊታችን" በሚልም የሻማ ማብራት መርሀግብር ተካሂዷል። ሰሜን እዝ ላይ ጥቅምት 24 2013 የደረሰበትን ጥቃት ለማስታወስ "አልረሳውም፤ እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ” በሚል በተለያዩ ሁነቶች ታስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም