ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱትን ከሃዲዎች ለማሸነፍ የዜጎች ሁሉ ትብብር ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱትን ከሃዲዎች ለማሸነፍ የዜጎች ሁሉ ትብብር ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱትን ከሃዲዎች ለማሸነፍ የዜጎች ሁሉ ትብብርና አብሮነት ወሳኝ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ገለፁ።
የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ለአገር መከላከያ ሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ደማቸውን ለግሰዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባላት እንደተናገሩት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱትን ከሃዲዎች ለማሸነፍ የዜጎች ሁሉ ትብብርና አብሮነት ወሳኝ ነው።
ሁሉም ባለው አቅምና ጉልበት ሰራዊቱን ለመደገፍ አካባቢውን ከመጠበቅ አንስቶ ግንባር ድረስ በመዝመት ለሰራዊቱ ያለውን አጋርነት ማሳየት አለበት ብለዋል።
የቀደምት አያቶች በከፈሉት መስዋእትነት፣ በደም እና አጥንታቸው የኖረችውን ኢትዮጵያ የአሁኑ ትውልድ የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበትም የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ፋናዬ መለሰ፤ የኢትዮጵያ የተለያዩ ችግሮችን በማሸነፍ እዚህ መድረሷን ገልፀው አሁንም ቢሆን የውጭ ጠላቶችም ሆኑ የውስጥ ባንዳዎች ጊዜያዊ ፈተናዎች እንጂ አሸናፊዎች አይሆኑም ብለዋል።
ሌላኛው የምክር ቤት አባል አምላዝ አሳሌ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱትን ከሃዲዎች ለማሸነፍ የዜጎች ሁሉ ትብብርና አብሮነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው የምክር ቤት አባል ሽፈራው ተሊላ፤ ኢትዮጵያ በተሻለ የለውጥ ሂደት ላይ መሆኗን ጠቅሰው አሁን የገጠመውን ጊዜያዊ ችግር በትብብር ልንመክተው ይገባል ብለዋል።