ቁጭቱ የኢትዮጵያውያንን አንድነትንና ህብረትን አጠናክሮታል

69

ሚዛን አማን፣ ጥቅምት 24/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ የፈጠረው ቁጭት የኢትዮጵያውያን አንድነትንና ህብረትን እንዳጠናከረው የደቡብ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ።

አሸበሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው የሀገር ክህደት ወንጀል ፈጽሞ የማይታሰብ ዘግናኝ ድርጊት እንደሆነ የሚዛን አማንና የዓርባ ምንጭ ከተሞች ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ድርጊቱ የአሸባሪው ህወሓት ያሰበውን እኩይ ዓላማ በማክሸፍ ኢትዮጵያዊነት በሰማዕታት መቃብር ላይ አብቦ እንዲያፈራ አድርጓል።

የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪው አቶ ወንድሙ ባይከዳ እንዳሉት ''በክስተቱ ሕዝቡ ጥልቅ ኅዘን ቢሰማውም፤ ከጫፍ እስከ ጫፍ ገንፍሎ በአንድነት በመውጣት ለመከላከያ ሠራዊቱ ያለውን ደጀንነት በተግባር አረጋግጧል።''

በተጨማሪም ''ለኢትዮጵያዊ አንድነትና ህብረት መልካም ዕድልን ፈጥሯል" ብለዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ኤልያስ ብርሃኑ እንዳሉት "የመከላከያ ሞት የእኛ ሞት በመሆኑ በተፈጠረብን ቁጭት ደም በመለገስና በገንዘብ አጋርነታችንን ስንገልጽ ቆይተናል።"

"ሀገር ከሌለች መኖር ስለማንችል ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለውን ጨፍጫፊ የህወሓት ቡድን በማስወገድ ሕልውናዋን እናስጠብቃለን" ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል።

ወጣት ኑሩ ከድር የጥፋት ቡድኑ ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልም ለማክሸፍ የተጀመረውን አንድነትና ትብብር ማጠናከር ወሳኝ ነው ብሏል።

"እንደ ሀገር ያጣነውን ሰላም መመለስ የምንችለው የጥፋት ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመተባበር ግብአተ መሬቱን መፈጸም ስንችል ነው" ብሏል።  

የኢትዮጵያን የጀግንነት ታሪክ ለማቆየት አሁን በገንዘብ ካደረገው ድጋፍ ባሻገር እስከ ግንባር ድረስ ለመዝመት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

የቤንች ሸኮ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጊስካር እንዳለት ድርጊቱ ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር በመነቃነቅ ከሃዲዎች ለማፍረስ የተመኟት ኢትዮጵያ በዜጎቿ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር መነሻ ሆኗል።

የዞኑ ሕዝብ መከላከያ ሠራዊቱን በመደገፍ ደጀንነቱን እያስመሰከረ መሆኑን ጠቁመው፣ የጥፋት ቡድኑ አስኪደመሰስ ድረስ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የጋሞ ዞን መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ኤደን ንጉሤ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው እኩይ ተግባር የኢትዮጵያን ሕዝብ በቁጭት ተነሳስቶ የአገሩን አንድነት እንዲጠበቅ አነሳስቶታል።

የዞኑ ሕዝብ ልጆቹ የመከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ ከማድረግ ባለፈ፤በገንዘብና በዓይነት ድጋፍ ያደረገው አገር አፍራሾችን ለመታገል ባለው ቁርጠኝነት ነው።

በዞኑ የመንግስት ሠራተኛው አቶ ኤልያስ ቦጋለ የኢትዮጵያ ሰላም ካልተረጋገጠ የሕዝቡ ህልውና ስለማይረጋገጥ የቡድኑን ግብዓተ መሬት ለማፋጠን መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ የሕዝብ ግንኙነትና ገጽታ ግንባታ ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ዳንኤል አረጋ ሕዝቡ ለአካባቢው ሰላም ዘብ በመቆም ለፀጥታ አካላት አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም