ወደቀያቸው ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን ተፈናቃዮች ገለጹ

86
ዲላ ነሀሴ 13/2010 ወደቀያቸው ተመልሰው ለመኖር ዝግጁ መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡ ተፈናቃዮች ገለጹ፡፡ ከጌዴኦ ዞን አጎራባች አካባቢዎች ተፈናቅለው በወረዳው ለቆዩት እነዚህ ዜጎች  ባህላዊ የምረቃና የሽኝት ስነስርዓት ተከናውኗል፡፡ ከቀርጫ ወረዳ የመጡት አቶ ጌታቸው በየነ በሰጡት አስተያየት " አካባቢው ተወልደን ያደግንበትና ንብረት ያፈራንበት በመሆኑ ለመመለስ ፍላጎት አለን" ብለዋል ፡፡ በሰላም ዕጦት ከሶስት ወር በላይ ከአካባቢያቸው ርቀው በመኖራቸው ሊጠቀሙበት ያልቻሉትን ማሳቸውን ለማልማት ዝግጁ እንደሆኑ ተናገረዋል፡፡ ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ መረጋጋትና በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን የተናገሩት አቶ ጌታቸው ጥፋተኞችን በሕግ ተጠያቂ የማድረጉ ተግባር በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቁመዋል ፡፡ ከዚሁ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ አብነት ዳንኤል በበኩላቸው ያሉበት የመጠለያ ሕይወት ለሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው አመቺ ባለመሆኑ ወደቀያቸው ተመልሰው ለመኖር ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል ፡፡ ሆኖም በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ ግለሰቦቸች በአፋጣኝ ተይዘው ለፍርድ የማይቀርቡ ከሆነ ዳግም ሥጋት እንደሚሆኑባቸው አመልክተዋል፡፡ ፡ " ሁላችንም የአባ ገዳዎችን ምክርና ተግሳፅ በመቀበልና ፈለጋቸውን በመከተል መንግስት እያቀረበ ላለው የመደመር ጥሪ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል "ብለዋል ፡፡ ከቢርቢርሳ ኮጆአ ወረዳ የተፈናቀለው ወጣት ጌታቸው በቀለ በሰጡው አስተያየት ወዳደገበት ቀዬው ለመመለስ ጉጉት እንዳደረበት ተናግሯል፡፡ " የጉጂና የጌዴኦ ወጣቶች መከፋፈሉን ወደጎን በመተው እንደ ጥንቱ ከአቶቻችን በወረስነው ፍቅርና አንድነት ተባብረን መኖር ይጠበቅብናል" ብሏል ፡፡ ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመመካከር የድርሻውን እንደሚወጣ የገለፀው ወጣት ጌታቸው ወደ አካባቢያቸው በሚመለሱበት ወቅት ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው አቅመ ደካሞችን እንደሚረዳም ገልጿል፡፡ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የገደብ ወረዳ ሻምበል አዛዥ ሻምበል ሲሳይ በሻ በአካባቢው የሰፈነው አንፃራዊ ሠላም ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል እየተታየበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ " በተፈጠረው ችግር ጥፋተኛ የሆነ አንድም ሰው የሚታለፍ የለም " ያሉት ሻምበል ሲሳይ በጉዳዩ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመያዝ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደየቀያቸው ሲመለሱ ደግሞ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጡ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስረድተዋል ፡፡ የጌዴኦ አባ ገዳ ደምቦቢ ማሮ ከጉጂ አባ ገዳ ጋር በመሆን ግጭቱን ለማስቆምና ዘላቂ ሠላም ለማምጣት በባህላቸው  መሰረት ዕርቅ ማድረጋቸውን አመልክተው " ጥፋተኞችን የመለየትና የመቅጣቱ ትግባር የመንግስት ነው" ብለዋል ፡፡ ሰዎች ወደየአካባቢያቸው ከተመለሱ በኋላም ከጉጂ አባ ገዳ ጋር በመሆን በያሉበት ስፍራ በመዘዋወር ዘላቂ ሠላም የማውረዱን ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎች በሚመለሱበት አካባቢ መልካም እንዲገጥማቸውና ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት በባህላዊ ሥርዐት በመመረቅ ህዝቡን አሰናብተዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም