በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ 28 ሺህ ሜትሪክ ቶን ቆሻሻ ለሃይል ማመንጫነት ውሏል

45
አዲስ አበባ ነሀሴ 13/2010 ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ 28 ሺህ ሜትሪክ ቶን ቆሻሻ ለሃይል ማመንጫነት ተጠቅሟል። ከደረቅ ቆሻሻ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጨው ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ማመንጫ ፕሮጀክት ኃይል ለማመንጨት በየዕለቱ የሚጠቀመውን 1ሺህ400 ቶን ደረቅ ቆሻሻ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያቀርባል። መዲናዋ በቀን ከምታመነጨው ከ3ሺህ በላይ ሜትሪክ ቶን ቆሻሻ ግማሹ ለሃይል ማመንጫነት እየዋለ ይገኛል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቆንጂት ደበላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከተማ አስተዳደሩ ሃይል ማመንጫው የሚያስፈልገውን የቆሻሻ አይነት በማቅረብ ሲሰራ ነበር። በዚህም ፕሮጀክቱ ሙከራ ባደረገባቸው ባለፉት ሁለት ወራት ከ28 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ተጠቅሟል። የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ፕላስቲክ፣ ወረቀትና ሌሎች ሊቃጠሉ የሚችሉ የቆሻሻ አይነቶችን ይፈልጋል። አፈር፣ ድንጋይና ዝቃጭ ቆሻሻ ፕሮጀክቱ ለሃይል ማመንጫነት እንደማይጠቀም የገለጹት ምክትል ስራ አስኪያጇ በነዚህና ሌሎች የአቅርቦት አሰራሮች ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል። ከተማ አስተዳደሩ ለሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ቆሻሻ የሚያቀርቡ ከ160 በላይ መኪኖችን አዘጋጅቶ ወደ ስራ ማስገባቱን ጠቁመዋል። ከሃይል ማመንጫው ከሚገኘው የአመድ ተረፈ ምርት በአመት ከ3 ሚሊዮን በላይ ለአገር ውስጥ ግንባታ የሚውል ብሎኬት እና ጡብ ማምረት ይቻላል። በዚህ ላይ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለብሎኬት ማምረቻ እንዲጠቀሙበት የሚደረግ መሆኑን ወይዘሮ ቆንጂት ገልጸዋል፡፡ ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአመት 200 ሺህ ቶን ስቲም ያመነጫል። በማጠራቀሚያ ሂደት ከቆሻሻው ዘቅጦ የሚወጣውን የተበከለና ቆሻሻ ውሃ ወደ ማጣሪያና ማከሚያ ክፍል በማስገባት በአመት ከ30 ሚሊዮን ሊትር በላይ የታከመና የተጣራ ውሃ በማቅረብ በመንገድ ዳር ለሚገኙ አትክልቶችና አስፓልት ማጠቢያ መጠቀም ይቻላል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም