ሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ልማትና ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል --- በደቡብ ህዝቦች ክልል የተሰማሩ ወጣቶች

75
ሀዋሳ ነሀሴ 13/2010 ሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ልማትንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ  መፍጠሩን  በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተሰማሩ ወጣቶች ገለጹ፡፡ ወጣቶቹ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ በተዘዋወሩባቸው ከተሞች የተደረገላቸው አቀባበል ትምህርት ሰጪና የኢትዮጵያ ህዝቦችን ማህበራዊ እሴቶች ጥንካሬ ያዩበት ነው፡፡ ከኦሮሚያ ክልል  ዱከም ከተማ የመጣው ወጣት ገመችስ ታደሰ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሜካንካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ ነው፡፡ በሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ በመሳተፉ ደስተኛ መሆኑን ገልፆ በሃዋሳ ከተማ የነበራቸውን የመጀመሪያውን ሳምንት መርሃግብር መጨረሳቸውን በሰጠው አስተያየት ገልጿል፡፡ በወልቂጤና ዱራሜ ከተሞችም በትምህርት፣ በመንገድ ደህንነት፣ በአከባቢ ጥበቃ፣ በችግኝ ተከላና በአከባቢ ጽዳት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ውጤታማ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር የተጀመረው ተግባር በተዘዋወሩባቸው የክልሉ  አካባቢዎች ነዋሪዎች ባደረጉላቸው አቀባበል መደሰቱን አመልክቶ " በለውጥ ውስጥ የራሳችንን አስተዋፅኦ እንድናበረክት እድል የፈጠረ ነው " ብሏል፡፡ ወጣት ገመችስ በሰጡት አገልግሎት ልማትንና ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ  መፍጠሩንም ተናግሯል፡፡ በወልቂጤ ከተማ ህዝቡ ባደረገላቸው  አቀባበልና ባሳያቸው  ፍቅር መደሰቷን የገለጸችው ደግሞ  ከትግራይ ክልል የመጣችው ወጣት ፋና ጴጥሮስ ናት፡፡ "ነዋሪዎቹ ለሰው ያላቸው ፍቅርና ስራ ወዳድነታቸው እጅግ አስደንቆኛልም "ብላለች፡፡ ከአማራ ክልል የመጣው ወጣት ይንገስ ፀጋዬ በበኩሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ብሄራዊ አንድነት ለማጠናከር እድል መፍጠሩን ተናግሯል፡፡ "በክልሉ በተዘዋወሩባቸው ከተሞች የተደረገላቸው አቀባበል ትምህርት ሰጪና የኢትዮጵያን ህዝቦች ማህበራዊ እሴቶችና ጥንካሬ ያየንበት ነው" ብሏል፡፡ ወጣቶች ጠቃሚ የህብረተሰብ ባህሎችን፣ እሴቶችን፣ ልምዶችንና የህይወት ተሞክሮዎችን እየቀሰሙ የኃላፊነት ስሜትን እንዲያዳብሩ ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ መነሻቸውን ሶዶና ሃዋሳ ከተማ አድርገው የተንቀሳቀሱ  ወጣቶቹ በወልቂጤ ከተማ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወናቸውን የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ክንፈ ፍቃዱ ገልጸዋል፡፡ የህዝብ ለሀዝብ ትስስርና  ኢትጵያዊነትን ከማጎልበት አኳያም ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን አመልክተዋል፡፡ በክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የወጣቶች ሰብዕና ልማት ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ቡላ በበኩላቸው በሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሳተፉት ወጣቶች 220 መሆናቸውን ተነግረዋል፡፡ ወጣቶቹ   በሀዋሳ፣  ወላይታ ሶዶ፣  አርባ ምንጭ፣ ወራቤ፣ ወልቂጤና ዱራሜ ከተሞች ተዘዋውረው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ትምህርት፣ አካባቢ ጥበቃ፣ የከተሞች ጽዳትና የመንገድ ትራፊክ ደህንነት አጠባበቅ፣ ለአረጋውያንና ለችግር የተጋለጠ ቤተሰቦችን መርዳት ወጣቶቹ ከተሰማሩባቸው ስራዎች መካከል ይገኙበታል፡፡ ከክልሉ 150 ወጣቶች በተመሳሳይ ተግባር ለመሳተፍ ወደ ሌላ የሀገሪቱ አካባቢዎች መሰማራታቸውንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም