ከኢትዮጵያ ጋር የኤሌክትሪክ ሃይል ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር አገሮች ወደ ስምምነት እየመጡ ነው

85
አዲስ አበባ ነሀሴ 13/2010 ኢትዮጵያ ካላት የኤሌክትሪክ ሃይል በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር አገሮች ወደ ስምምነት እየመጡ እንደሆነ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ዛሬ የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምርቃት ላይ እንደገለጹት፤ መንግስት በታዳሽ ሃይል ልማት በምስራቅ አፍሪካ የሃይል ትስስር ለመፍጠር በስፋት እየሰራ ነው። ቀደም ሲል ለሱዳንና ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ሃይል በመሸጥ በአመት በአማካኝ 75 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉንም ጠቅሰዋል። ከሁለቱ አገሮች በተጨማሪ ከኬንያ፣ ታንዛንያና ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመጠቀምና የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ፍላጎት በማሳየት ወደ ስምምነት እየመጡ እንደሆነ ተናግረዋል። በቀጣይ ለነዚህና ሌሎች አገሮች በቂ የኤሌክትሪክ ሃይል በማቅረብ ዘርፉን የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል። በአሁኑ ሰአት ከወላይታ ሶዶ እስከ ኬንያ እየተዘረጋ ያለው ኢትዮ-ኬንያ ባለ500 ቮልት ከፍተኛ የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ  በኢትዮጵያ በኩል ያለው ተጠናቆ በኬንያ በኩል ያለው መስመር ግንባታ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር በአፍሪካ እውን እየሆነ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሩ ከአፍሪካ የእርስ በእርስ ትስስር ከመፍጠሩ ባሻገር የአለም አቀፍ የኢነርጂ ትስስር እንዲፈጠር ኢትዮጵያ የቀዳሚነት ሚና ልትጫወት የምትችልበት ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል። በኤሌክትሪክ አቅርቦትና መቆራረጥና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከውሃ 50 ሺህ ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት፣ ከእንፋሎት 10 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ እንዲሁም 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜጋ ዋት ከታዳሽ ሃይል ማልማት እንደምትችል ጥናቶች አረጋግጠዋል። በአሁኑ ሰአት አገራዊ የማመንጨት አቅም 4300 ሜጋ ዋት የደረሰ ሲሆን በሁለተኛው የእድገና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 17 ሜጋ ዋት ለማድረስ እየተሰራ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም