ሀገሪቱን ለማፍረስ እየጣረ ያለውን አሸባሪ ቡድን ለመፋለም ተዘጋጅተናል

125

ሐረር፤ ጥቅምት 23/2014(ኢዜአ) ሀገሪቱን ለማፍረስ እየጣረ ያለውን አሸባሪ ቡድን ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ለመፋለም መዘጋጀታቸውን የሐረሪ ክልል ወጣቶች አስታወቁ።

አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት የአፋርና አማራ ክልል ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ በመሆኑ ለመታገል መነሳሳታቸው ወጣቶቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

በክልሉ የሶፊ ወረዳ ነዋሪ  ወጣት ኩበዬ ባባ፤ በአሁኑ ወቅት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሀገሪቱ ላይ የከፈተው  ጦርነት ነገም ሐረር ላይ የማይደርስበት ምንም ምክንያት ስለሌለ ጉዳዩ የአፋርና የአማራ ነው ብለን መቀመጥ የለብንም ነው ያለው።

ጠላት በህዝብ ማዕበል በመደራጀት ሀገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክቶ፤ በመደራጀትና አንድነትን በማጠናከር የሽብር ቡድኑን መደምሰስ እንደሚገባ ተናግሯል።

መከላከያን በመደገፍ ጠላትን ለመደምሰስ ዝግጁ ነኝ ብሏል ወጣቱ።

የአሸባሪው የህወሓት ቡድን እቅድ  የአማራ እና አፋር ክልልንን መውረርና  ማፍረስ ሳይሆን  አገርንና ህዝቡን ለመበታተን መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት ከድር ዩስፍ ነው።

ይህን የጥፋት ቡድን ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ለመፋለም መዘጋጀቱን አስታውቋል።

ወጣት አነስ መሐመድ በበኩሉ፤ የሽብር ቡድኑን በመደምሰስ ሀገርን ለማዳን ሁሉም አካል በህብረት ሊቆም እንደሚገባ አመልክቷል።

''በዚህም ወጣቱ የሽብር ቡድኑን የሃሰት ፕሮፖጋዳ ሳይሰማ ከመቼውም ጊዜ በላይ አካባቢውን በትኩረት መጠበቅ ይኖርብናል፤ እኔም እንደ አንድ ወጣት ሀገሬን ለማዳን ዝግጁ ነኝ'' ሲል አስታውቋል።

ኢትዮጵያን ለመታደግ  ሁሉም ዜጋ በጋራ በመሆን ወራሪ ሃይሉን መደምሰስ እንዳለበት የተናገረው ደግሞ ነቢል መሃመድ ነው።

''እኔም መንግስት በሚያቀርብልኝ ጥሪ በመሰማራት መሰዋዕትነት ከፍዬ ሀገሬን ለማዳን ዝግጁ ነኝ'' ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም