ሰራተኞች የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የአገሪቱን ህግ አክብረው ይሰራሉ

85

ጥቅምት 22/2014 (ኢዜአ) የዩኒሴፍ ሰራተኞች የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የአገሪቱን ህግ አክብረው እንደሚሰሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት  የምስራቅ እና የደቡብ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር መሀመድ ኤም. ማሊክ ፎል ገለጹ።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት  (ዩኒሴፍ) የምስራቅ እና የደቡብ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ሚስተር መሀመድ ኤም. ማሊክ ፎል ጋር ተወያይተዋል።

በዉይይታቸዉ ወቅት ሚስተር መሀመድ ኤም. ማሊክ ፎል ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በማህበራዊ ልማት ዘርፎች የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታዉሰው፣ በተለይም በህፃናት እና ታዳጊ ልጃገርዶች እና ሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዳይሬክተሩ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በመንግስት ከአገር እንዲወጡ በተደረጉት የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ምትክ ሌላ ለመላክ እንዲቻል ከመንግሥት ጋር ምክክር ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የአገሪቱን ህግ አክብረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ዩኒሴፍ በበኩላቸው የድርጅቱ ሰራተኞች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እሴቶችን እና የሀገሪቱን ህግ በማክበር ተግባራቸውን መፈፀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ባለልዩ መብት ድርጅቶች ጋር የረጅም ጊዜ ቁርኝት ያላትና ለባለብዙ ወገን ግንኙነት የተለየ ትኩረት የምትሰጥ መሆኑ አውስተው፣ መንግስት ከድርጅቱ ጋር በቅርበት እና በትብብር ጋር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ዩኒሴፍ የመንግስትን ጥረት በመደገፍ በጤና፣ በትምህርት፣ በንፁህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት፣ በሌሎች የማህበራዊ ልማት ተግባራት የሚያከናዉነዉን ስራ አድንቀዋል።

በተጨማሪም በአገራችን የተለያዩ ክልሎች በተከሰቱ የተፈጥሮ እና ሰዉ ሰራሽ አደጋዋች ህፃናት እና ሴቶች ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት በመንግስት በኩል አስፈላጊው እገዛ ይደርጋል ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት ከ60 ዓመት በላይ በኢትዮጵያ በማህበራዊ ልማት ዘርፎች የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ከተልዕኳቸው ውጪ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ የዩኒሴፍ ሰራተኞችን ጨምሮ 7 የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ተወካዮች ከአገር እንዲወጡ መደረጋቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም