መንግስት የሚያራምደው ሰላምና ማህበረሰባዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ራዕይ ህገ ወጥነትን የማይታገስ ነው-- ዶክተር ዐቢይ አህመድ

90
ባህርዳር ነሀሴ 13/2010 " መንግስት እንደ እሴት የሚያራምደው ነጻነት፣ ሰላምና ማህበረሰባዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ራዕይ ህገ ወጥነትንና አመጽን የማይታገስ ነው "ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወረዳ እስከ ክልል ከሚገኙ የብአዴን መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች ጋር በባህርዳር ከተማ እየተወያዩ ነው። በውይይቱ ወቅት ዶክተር ዐቢይ አህመድ  እንደገለጹት የሀገሪቱ  ህዝቦች ለህግ የበላይነት መገዛት ዘመን ተሻጋሪ እሴት ያላቸው መሆኑን በስነ ቃሎቻቸው ጭምር የሚስተዋል ነው። ለዘመናት የዘለቀ የስልጣኔ ባለቤት የሆነችው አትዮጵያ  የመንግስት መዋቅርና ስርዓት በመዘርጋት በህዝቦቿ ዘንድ ፍትህና ርትዕ የሰፈነባት ሀገር ናት። ባለፉት አራት ወራት ሀገራዊ  አንድነትንና ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብን በማጎልበት አመርቂ ውጤት እየታየ መምጣቱን ተናግረዋል። " በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ሪፎርም የይቅርታ፣ የነጻነትና የፍትህ  ፋና ወጊ ስራዎቻችንን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚገኙ ዜጎቻችን ተስፋን ያጎናጸፈ ነው" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳመለከቱት ህግን እንደመሳሪያ በመጠቀም በስልጣን የመቆየት አካሄድ ያመጣቸውን መዘዞች ለማረም ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል ያለአግባብ  ይወነጀሉ የነበሩ ዜጎችና የፖለቲካ ቡድኖች በይቅርታና በምህረት እልባት እንዲያገኙ ተደርጓል። በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን በማቀራረብ ለአንድ ሀገራቸው ልማት፣ ብልጽግናና እድገት የሚሰሩበት እድል ከምንጊዜውም በላይ ምቹ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ለኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ፍትህ የሚደረገው ትግል ከማህበረሰቡ የሞራልና የኃይማኖት እሳቤዎች ጋር ተዋህዶ እንዲዘልቅ ከኃይማኖት አባቶች፣ ከምሁራንና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተቀራርቦ መስራት ተጀምሯል፡፡ ሆኖም የህዝቡን ዘርፈ ብዙ ፍላጎቶች በአንድ ጀምበር ማሟላት የሚቻል ባይሆንም በፈጣን ተስፋ ሰጪ መዘውር ውስጥ የተገባ በመሆኑ እንደ ሃገር መውደቅም ሆነ ወደ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አሰራሮች መመለስ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል። "መንግስት እንደ እሴት የሚያራምደው ነጻነት፣ ሰላምና ማህበረሰባዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ራዕይ ህገ ወጥነትንና አመጽን የማይታገስ ነው" ብለዋል። የዜጎች መብት፣ ነጻነትና ፍትሃዊነት በማረጋገጥ የአካል፣ የህይወትና የኑሮ ዋስትናቸውን ለማስጠበቅ ህግንና ህገ መንግስታዊ ስርዓትን በሙሉ አቅም ማስከበር ግድ ይላል። የመንግስት የጸጥታ አካላትና አመራሮችም የህግ የበላይነት በግለሰቦችም ሆነ በቡድኖች ሲጣስ በቸልታ ማየት እንደሌለባቸው አሳስበዋል። በተለይም የግልና የቡድን ጥቅሞቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ማስጠበቅ እየቻሉ ከዚህ በተቃራኒው በመሄድ  ወንጀልን ለመፈጸም የሚያስቡ አካላት ከድርጊታቸው መታቀብ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። ህዝብን ከህዝብ እያጋጩ ጸጥታን በማደፍረስ በህገወጥ ድርጊት ተሰማርቶ የተገኘና በማንኛውም መልኩ የተባበረ አካል ላይ መንግስት ህግን ተከትሎ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆኑንም አስታውቀዋል። ከ2ሺህ በላይ የብአዴን መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች በተሳተፉበት የውይይት መድረክ  ጠቅላይ ሚንስትሩ የመነሻ ጽሁፍ አቅርበው ተሳታፊዎች በሚያነሷቸው  ጥያቄዎች ላይም ማብራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም