በኢትዮጵያ የሚከናውነው የነዳጅ ልማት ዳር እስኪደርስ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ የደቦይን ወረዳ ነዋሪዎች አረጋገጡ

123
ጂግጂጋ ነሓሴ 13/2010 ኢትዮጵያ የምታከናውነው የነዳጅ ልማት ፕሮጀክት ዳር እስኪደርስ ከመንግስት ጎን ቆመው የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ በሶማሌ ክልል የደቦይን ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ። በወረዳው እየተከናወነ ያለው የድፍድፍ ነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት መንግስት በአገሪቱ እያከናወናቸው ካሉት ግዙፍ ልማቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ያለምንም ፋታ በቀን ለ24 ሰዓት እየተሰራ ይገኛል። ኢዜአ በፕሮጀክቱ ተገኝቶ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ በስፍራው ከሚገኙ የፌዴራልና የክልል ጸጥታ አካላት ጋር በመስራት ለፕሮጀክቱ እውን መሆን ድርሻቸውን እየተወጡ ነው። ወይዘሮ ሃሊማ ሲጋል ፕሮጀክቱ በአካባቢያቸው እንደመገኘቱ የወረዳው ህዝብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ዳር እስኪደርስ  የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ይናገራሉ። አገራቸው ፕሮጀክቱን አጠናቃ በኢኮኖሚ እራሷን ችላ ማየት ምኞታቸው እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ አቶ በሽር ማልን ናቸው። ይህ እውን እስኪሆን የወረዳው ህዝብ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። አቶ በሽር በፕሮጀክቱ እዚህ መድረ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ የአካባቢያቸውን ሰላም ስለማስጠበቅ ነቅተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። የፕሮጀክቱ ከፍተኛ መሃንዲስ ግርማ ካሳይ በበኩላቸው ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተቀናጅተው በመስራታቸው ፕሮጀክቱ ለአፍታም ሳይቋረጥ እየተከናወነ መሆኑን ይናገራሉ። የፕሮጀክቱን እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ሲጎበኙ ያገኘናቸው በአገር መካላከያ ሚኒስትር የኢንዶክትርኔሽን ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል መሃመድ ተሰማ የአካባቢው ህብረተሰብ ከጸጥታ ሃይል ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ለፕሮጀክቱ መሳካት የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቁመዋል። ፕሮጀክቱም በተቀመጠለት አግባብ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም