ብአዴን የሚያካሄደው ጉባኤ ለህዝብ ጥቅም በፅናት የሚታገሉ ጠንካራ አመራሮች የሚደራጁበት እንደሚሆን አስታወቀ

105
ባህርዳር ነሀሴ 13/2010 የብሔር አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የሚያካሄደው መደበኛ ጉባኤ የአማራ ህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በፅናት የሚታገሉ ጠንካራ አመራሮች የሚደራጁበት እንደሚሆን የድርጀቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ ትናነት እንደገለጹት ድርጅቱ በመጪው መስከረም ወር አጋማሽ በሚያካሄደው 12ኛው መደበኛ ጉባኤ የፖለቲካና የድርጅት ስራዎች በጥልቀት ይገመግማል። በጉባኤውም ድርጅቱ ሲመራበት በቆየው ርዕዮተ አለምና መተዳደሪያ ደንቡ ላይ በመወያየት  ማሻሻያዎች እንደሚደረጉም ተናግረዋል። በጉባኤውም የአማራን ህዝብ ፍላጎት ተረድቶ የሚመራ አዲስ ማዕከላዊ እና የስራ አስፈፃሚ  እንዲሁም  የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚቴዎች ምርጫ ይካሄዳልም።  የአማራን ህዝብ ከምንም በላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎችን በትክክል ተገንዝቦ በፅናት ታግሎ የሚፈታ አመራር እንደሚደራጅም አስታውቀዋል።  " በየደረጃው ያለውንና ህዝቡን ክፉኛ ያማረረውን የመልካም አስተዳደር ችግር  የመፍታት ብቃት ያለው ተራማጅ አመራር ድርጅቱን እንዲመሩ ይደረጋልም "ብለዋል። በተለይም ድርጅቱ የሚታገልለት የአማራ ህዝብ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲጓዝ የሚያስችል የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲሆንም ይፈለጋል። በጉባኤው ነባርም ሆነ አዲስ አመራር ለውጡን ለመምራትና ተሸክሞ ወደፊት አብሮ የመጓዝ ብቃት ያለው እንዲሆን እንደሚመቻች እንደሚደረግ ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ ለጉባኤ ግብዓት ለማሰባሰብና በአሁኑ ወቅት እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ በተሻለ አመራር አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲሁም የአማራን ህዝብ ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዝ ኮንፈረንስ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም