በኦሮሞ ህዝብ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች በፌደሬሽን ለመዋሃድ ውይይት ጀመሩ

60
አዲስ አበባ ነሓሴ 13/2010 በኦሮሚያ ክልል በህዝብ ስም የተደራጁ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ላይ ቢዋሃዱ ተፎካካሪነታቸው ሊጨምር እንደሚችል የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ ገለፀ። ፓርቲው በኦሮሚያ ክልል ህዝብ ስም ከተደራጁ ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት ለመፍጠር ባደረገው ጥሪ መሰረት ጥሪውን ተቀብለው ወደ ውይይት መድረክ ከመጡት ጋር ውይይት ማድረግ ጀምሯል። የዛሬው የውይይት መድረክ ፓርቲዎቹን ወደ አንድ ሊያመጣ የሚችል የፖለቲካ ፕሮግራምና አቅጣጫ ላይ መነሻ ሊሆን የሚችል ሰነድ ቀርቧል። በሰነዱ እንደተገለፀው፤ አሁን ላይ በኦሮሞ ስም የተደራጁ ከ15 በላይ ፓርቲዎች ቢኖሩም በተናጠል ያላቸው አቅም ተፎካካሪነታቸውን ሊያጎላ የሚችል አይደለም። የፓርቲው ሊቀመንበር አባ ገዳ ሮበሌ ታደሰ እንዳሉት፤ ፓርቲዎቹ በጋራ ተዋህደው ቢመጡ የኦሮሞን ህዝብ መብትና ጥቅም ማስጠበቅ ይችላሉ። በተጨማሪም ''በኦሮሚያ ክልል ብቻ በተያዩ ስያሜዎች ከ14 የማያንሱ ሰንደቅ አላማዎች የሚታዩ ሲሆን የኛ ወደ አንድ መምጣት አንድ ሊወክል የሚችለውን እንድንመርጥ እድል ይሰጣል'' ብለዋል። በሌላ በኩል ፓርቲዎቹ በምርጫ የሚያገኙት የተበጣጠሰ ድምፅ ውህደቱ ቢፈጠር ተደምሮ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል። በሰነዱ እንደተመላከተው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደአንድ ቢመጡ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት ለማምጣትና የመደመር ጉዞውን ስኬታማ ለማድረግ ያስችላል። ሰነዱን ተከትሎ ተሳታፊ የነበሩት ፓርቲዎች በሰጡት ሃሳብ ውህደቱ ቢፈጠር ከሁሉም የተውጣጣ የተጨመቀ ሃሳብ ስለሚገኝ የተሻለ ፕሮግራምና አቅጣጫ ይዞ መቅረብ ይችላል ብለዋል። በዛሬው የውህደት መነሻ ውይይት ላይ የኦሮሚያ አንደነትና ነጻነት ድርጅትን ጨምሮ 4 ፓርቲዎች ተገኝተዋል። ዛሬ ካልተገኙ ፓርቲዎች ጋር ሳምንት ተመሳሳይ ውይይት እንደሚደረግም ተጠቁሟል። በቀጣይ ሁለት ሳምንትም የማጠቃለያ ሰፊ ውይይት ፈቃደኝነታቸውን ከሚያሳዩ ፓርቲዎች ጋር በኦሮሚያ ባህል ማዕከል እንደሚደረግ አባ ገዳ ሮበሌ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም