በበጀት ዓመቱ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል-በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዳሴ ግድቡ ማስተባበሪ ጽህፈት ቤት

90
ነሐሴ 13/2010 በተያዘው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ በጊዜያዊነት መታቀዱን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዳሴ ግድቡ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የመዲናዋ ነዋሪ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ተጠይቋል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ዘውዴ ገብረኪዳን ለኢዜአ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ በጊዜያዊነት የታቀደው 160 ሚሊዮን ብር ካለፈው ዓመት አፈጻጸምና ከህብረተሰቡ ተነሳሽነት አንጻር ተከልሶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይጀመራል፡፡ በ2010 በጀት ዓመት በቦንድ ግዢ እና በስጦታ 152 ሚሊዮን 350 ሺህ ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ200 ሚሊዮን 800 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡን ያስታወሱት ኃላፊዋ ይህም የመዲናዋ ነዋሪ ለግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለው ድጋፍና ተነሳሽነት የተሻለ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡ ኃላፊዋ እንዳብራሩት የታቀደውን ገቢ ለመሰብሰብ ያመች ዘንድ በየበጀት ዓመቱ አንድ ጊዜ ብቻ ይካሔድ የነበረውን የቦንድ ሳምንት በተለያዩ ጊዜያት ለማካሔድና 538 ሺህ 417 የመዲናዋ ነዋሪዎችን ተሳታፊ የሚያደርግ 304 የንቅናቄ መድረክ ለማዘጋጀት እቀድ ተይዟል፡፡ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ቃል የተገባውን ገንዘብ በወቅቱ ከመሰብሰብ ጋር በተያያዘ የአመራሩ ክትትልና ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑ ቃል የተገባው ገንዘብ በወቅቱ እየተሰበሰበ አለመሆኑንም ነው ኃላፊዋ ያብራሩት፡፡ ህብረተሰቡ የግድቡ መሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ እያሳየ ያለውን የሞራል፣ የገንዘብ፣ የዲፕሎማሲ፣ የቁሳቁስና የእውቀት ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ጠይቀዋል፡፡ ኢንጅነር ከፈለኝ ተምትሜ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከወር ደሞዙ ቦንድ እየገዛ መሆኑን ገልጾ የፕሮጀክቱ ስራ እስኪያጅ ሞት በቁጭት ድጋፉን ለማጠናከር እንዳነሳሳው ተናግሯል፡፡ ከገንዘብ ድጋፉ ባሻገር በሙያውም ቦታው ድረስ ሔዶ የማገልገል ፍላጎትና ቁርጠኝነት እንዳለው ነው የተናገረው፡፡ የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያው ብዙአየሁ ረታ ህብረተሰቡ ስለ ግድቡ በቂ መረጃና ግንዛቤ እንዲኖረው የሚያደርጉ ስራዎችን ከመስራት በተጓዳኝ የገንዘብም ሆነ የጉልበት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ የግድቡ መሰረት ደንጋይ ከተቀመበት ጊዜ ጀምሮ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ከህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጸህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም