በጤናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ ርብርቡ ይጠናከራል

75

ጂግጂጋ ፤ ጥቅምት 20/2014(ኢዜአ) በሁለተኛው ዙር የጤና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም የመጀመሪያ ዓመት ላይ የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር ዘንድሮ የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ ርብርቡ እንደሚጠናከር የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ሚኒስትሯ በጂግጂጋ ከተማ እየተካሄደ ባለው  የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ  እንዳሉት፤ ባለፈው ዓመት ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎትን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግቧል።

ኮሮናን በመከላከል ፣  ዘመናዊና ፈጣን መመርመሪያ እና ክትባት  ተደራሽ በማድረግ፣የእናቶች እና ህፃናት ጤና በመጠበቅ ፣ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል እና ህክምና ተደራሽ በማደረግ ጥሩ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

የህፃናት መቀንጨርን ለመከላከል በስርዓተ ምግብ መርሃ ግብር የተከናወኑ ስራዎች ጅምር ውጤት የመጣባቸውና የሚጠናከሩ ይሆናሉ ነው  ያሉት ዶክተር ሊያ።

ሆኖም የኮሮና  ቫይረስ ወረርሽኝና በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈጠሩ ችግሮች  በዘርፉ ስራዎች ላይ ጫና መፍጠራቸውን  አንስተዋል።

እንደ ሚኒስትሯ   ገለፃ ፤ በሁለተኛው ዙር የጤና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም የመጀመሪያ ዓመት ላይ  የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር ዘንድሮ  የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ ርብርቡ ይጠናከራል ።

በተጨማሪም የማህበረሰብ ጤና መድህን ተደራሽነት የማስፋት፣ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎትን ፣የእናቶችና የህፃናት ጤና ለመጠበቅ፣የህብረተሰቡን የጤና ፍላጎት ለማሟላት ፣የአእምሮ ጤና አገልግሎት ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የማከም ስራ በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።

በጉባኤው ላይ መንግስት የጤና ተደራሽነትና ጥራትን ለመጠበቅ የሚያከናውናቸው ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ አለምአቀፍ ለጋሽ ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር  አቶ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው፤ በክልላችን የሚገኘው  አርብቶ አደር የጤናው ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወኑ ስራዎች  ውጤት ቢመጣም  አኗኗር መሠረት ያደረገ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋትና ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ማረጋገጥ ይጠበቅብናል ብለዋል።

እንደ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገለፃ፤  የኮሮና ወረርሽኝ በክልሉ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ።

ክልሉ ከጎረቤት ሀገራት ሰፊ ድንበር የሚጋራ በመሆኑ ወረርሽኙን ለመከላከል የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል  ብለዋል።

በተጨማሪም በክልሉ የእናቶች እና ህፃናት ጤና በመጠበቅ፣የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እንዲስፋፋ ፣ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ትርጉም ባለው መንገድ ለመከላከል እንቅስቃሴ መጀመሩንም አመልክተዋል።

በዚህ ላይ  የሚፈለገው ውጤት እንዲመዘገብ የጤና ሚኒስቴርና ሌሎች የዘርፉ አጋር አካላት  ዕገዛቸውን እንዲያጠናክሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በ23ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ጤና ሚኒስቴር  በህይወት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት ፣በሙያው መስክ  የተሻለ   ስራና አገልገሎት እንዲሁም በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ጥሩ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ባለሙያዎችና አመራሮች የሜዳሊያ፣ ዋንጫና  የዕውቅና  ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በሱማሌ ክልል አውበሬ ገጠራማ ቀበሌ ጤና ጣቢያ የማህፀን እና የፅንስ ስፔሻሊስት ሆነው ህዝብን በመገልገል ላይ የሚገኙት ዶክተር  ዋለልኝ አንተንብዬ  የዓመታዊ ጉባኤው ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል፤ ክልሉም ሸልሟቸዋል።

ባለፈው ዓመት በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ አበይት ተግባራት የተመላከተ የፎቶ ግራፍ እና የአኃዛዊ መግለጫዎች  አውደ ርዕይ ተከፍቶ እየተጎበኘ ይገኛል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም