በወንጀሎችና ሰላምን በማደፍረስ እኩይ ተግባራት የሚሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

58
አዲስ አበባ ነሐሴ 13/2010 በወንጀሎችና ሰላምን በማደፍረስ እኩይ ተግባራት የሚሰማሩ አካላት ከድርጊታችሁ እንዲቆጠቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ። ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢዜአ በላኩት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ የግልና የቡድን ጥቅም ለማስጠበቅ በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ እየተቻለ በተለያዩ ወንጀሎችና ሰላምን የማደፍረስ እኩይ ተግባር ላይ ላይ ለመሰማራት የሚያስቡ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል። የህዝብን ፀጥታ በሚያደፈርሱና ህዝብን ከህዝብ በሚያጋጩ ህገወጥ ተግባራት ላይ የሚሰማራና የሚሳተፍ እንዲሁም ለህገወጥ ተግባራት ተባባሪ የሚሆን አካል ላይ ህግን ተከትሎ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል። በነፃነት ስም የመንጋ ፍትህ በማራመድ የህግ የበላይነትን የሚፈታተኑ አካላት ላይ መንግስት አስፈላጊውን ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ አገሪቱ የመንግስት አወቃቀር ስርዓት የፍትህ አሰጣጥ እውቀትና ለነፃነትም ምሳሌ የሆነች አገር ብትሆንም አሁን ላይ የመንጋ ፍትህ (ሞብ ጀስቲስ) እየተበራከተ መጥቷል። ቀደም ባሉት ዓመታት ይስተዋል የነበረውን ሕግን እንደመሣሪያ ተጠቅሞ የመግዛት አካሄድ ያመጣቸውን መዘዞች ለማረም አላግባብ የታሰሩትን የመፍታት፣ ይቅርታና ምህረት ተደርጓል ነው ያሉት። ይህን ነፃነትና ስርዓት አልበኝነትን በውል ባለመለየት ህግን የጣሱ እንቅስቃሴዎችና ድርጊቶች እየተበራከቱ መጥተዋል። ድርጊቶቹ በአንድ ክልል ብሔርና ቋንቋ ወይም ኃይማኖት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ስፍራዎችና ብሔረሰቦች ላይ የሚታዩ ናቸው። እንዲህ ያሉት እንቅስቃሴዎች የዜጎችን ደህንነትና የአገሪቱን ሰላም በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑ ከመሆናቸውም ባለፈ ለዘመናት የኖረ የአብሮነትና መቻቻል መልካም እሴትን እየናደ መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም እነዚህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡ በመንጋ የሚሰጡ የፍትህ እርምጃዎች እንደ አገር ለመቀጠል አሳሳቢ እንደሆኑ እና በፍጥነትም መታረም እንዳለባቸው መንግስት በጥብቅ ያምናል። ድርጊቶቹ በጥቂት ግለሰቦችና አካላት በዘፈቀደና በስሜት የሚፈፀሙ በአመዛኙ የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረጉ አካላዊ ጥቃቶች፤ ግድያዎች፤ የንብረት ውድመቶችና መፈናቀሎች የሕዝቡን ሰላም፤ ነፃነትና የኑሮ ዋስትና ከመሰረቱ እያናጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። ''የግልና የቡድን ጥቅሞቻችሁን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማስጠበቅ እየቻላችሁ በተለያዩ ወንጀሎችና ሰላምን የማደፍረስ እኩይ ተግባራት ላይ ለመሰማራት የምታስቡ አካላት ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ'' ሲሉም ጠይቀዋል። ሆኖም የህዝብን ፀጥታ በሚያደፈርሱና ህዝብን ከህዝብ በሚያጋጩ ተመሳሳይ ህገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርቶ የተገኘ እንዲሁም ለእንደዚህ አይነት ህገወጥ ተግባራት በምንም መልኩ ትብብር ያደረገ አካል ላይ ህግን ተከትሎ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መንግስት ቁርጠኛ እንደሆነ በጥብቅ አሳስበዋል። በኢትዮጵያ ዘላቂ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንዲፋጠን፤ በሕግ የበላይነት እና በህዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ መገንባት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል። የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡት መግለጫ ሙሉ ቃል
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም