በሶማሌ ክልል የተፈጠረው ሁከት ያስከተለውን ቁርሾ በማስወገድ ለሰላምና አብሮነት በጋራ እንደሚሰሩ የጂግጂጋ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ

65
ጂግጂጋ ነሀሴ 13/2010 በሁከት ምክንያት የተከሰተውን ቁርሾ በማስወገድ ለሰላምና አብሮነት በጋራ እንሰራለን ሲሉ በሶማሌ ክልል የጂግጂጋ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ። በጂግጂጋ ከተማ በዛሬው ዕለት ህዝባዊ ጉባዔ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በጉባዔው ላይ የተሳተፉ የዞኑ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፤ ሁከቱ ያስከተለውን ቁርሹ በማስወገድ ለሰላም መረጋገጥና ለአብሮነት መዳበር በጋራ ይሰራሉ። በህዝባዊ ጉባዔው በርካታ ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በክልሉ ሲፈጸሙ የነበሩ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶችን የሚያወግዙ ሃሳቦችን አንጸባርቀዋል። ከሳምንታት በፊት በክልሉ ተከስቶ የነበረውን ሁከትና ዝርፊያ ያወገዙት ነዋሪዎቹ ድርጊቱ የፈጠረውን ቁርሾ በማስወገድ ለሰላምና ለአብሮነት ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ በመደገፍ ለልማትና ዕድገት የድርሻቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል። በክልሉ በተከሰተው ሁከትና በተፈጸመው ዝርፊያ ተሳታፊ የነበሩ አካላት በአስቸኳይ ለህግ ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑ መሰራት እንዳለበትም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። በጉባዔው ላይ የተገኙት በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የመረጃ ዋና መምሪያ  ኃላፊ ሌተናል ጀኔራል ሃሰን ኢብራሂም በበኩላቸው የሰላሙ ባለቤት ህዝቡ ራሱ በመሆኑ ሁሉም የክልሉ ነዋሪ ሰላሙን ለማስጠበቅ በትጋት እንዲሰራ ጥሪ አስተላልፈዋል። በጉባዔው ላይ ከዞኑ ነዋሪዎች በተጨማሪ በክልሉ ሲፈጸም የነበረውን የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብት ጥሰት ለመከላከልና ለማውገዝ በተለያየ መንገድ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ወገኖች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም