የ"አጎዋ" ስምምነት በኢንዱስትሪ ፓርኮች የስራ ዕድል ለተፈጠረላቸው ሠራተኞች በጎ አስተዋጽኦ አለው

87

ጥቅምት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ ሀገራት ምርታቸውን ከቀረጥና ኮታ ነጻ ወደ አሜሪካ ገበያ እንዲያስገቡ የሚረዳው የ"አጎዋ" ስምምነት በኢንዱስትሪ ፓርኮች የስራ ዕድል ለተፈጠረላቸው ሠራተኞች በጎ አስተዋጽኦ እንዳለው መገንዘባቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ገለጹ።

በአምባሳደሯ የተመራ ልዑክ ዛሬ  የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን  ጎብኝቷል።

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደሯ ገልጸዋል።

ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በአፍሪካ በጨርቃ ጨርቅ ምርቶች በመንግስት የተገነባ የመጀመሪያ ፓርክ መሆኑን እንደሚያውቁ  ተናግረዋል።

በፓርኩ የአሜሪካው "ፒ.ቪ.ኤች" ካምፓኒን ጨምሮ በርካታ አምራች ኩባንያዎች ያሉበት እንደሆነም መረዳታቸውን ገልጸዋል።

በፓርኩ ውስጥ በርካታ ሴቶች የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን በመመልከታቸው መደሰታቸውን የገለጹት አምባሳደሯ፤ የስራ እድሉ የተፈጠረላቸውን ሴቶች በአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት በኩል መደገፍ ስለሚቻልበት ሁኔታ መምከራቸውን ተናግረዋል።

በተለይ አሜሪካ ከሰሀራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት የፈቀደችው ምርታቸውን ከቀረጥና ኮታ ነጻ ወደ አሜሪካ ገበያ እንዲያስገቡ የሚረዳው የ"አጎዋ" ስምምነት በሠራተኞቹ ህይወት ላይ ስላለው በጎ አስተዋጽኦ የበለጠ ግንዛቤ ማግኘታቸውን አብራርተዋል።

የፓርኩ ሠራተኞች በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ደስተኛ መሆናቸውን መስማት ያስደስታል" ያሉት አምባሳደሯ፤ በሰራተኞቹ ህይወት ላይ የተፈጠረውን ለውጥ ማጠናከር ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በነበራቸው ቆይታም የተማሪዎችን የሠላም ክበብ የጎበኙ ሲሆን ተማሪዎች የእርስ በርስ ግንኙነትና ሰላምን ለማጠናከር እያደረጉት ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

በምርምርና ጥናት ሥራዎች ከዩኒቨርሲቲው ጋር ለመስራት በሚያስችሉ ሁኔታዎችና ቀጣይ ግንኙነቶች ላይ መወያየታቸውንም አመልክተዋል።

በውይይቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና ምሁራን ተገኝተዋል።

አምባሳደር ጊታ ከዚህ ቀደም በትግራይ፣ አማራ፣ ሱማሌ እና ደቡብ ክልሎች ጉብኝት በማካሄድ የአገራቸውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎና አጋርነትን ለማሳደግ የሚረዱ ውይይትችን እንዳደረጉ አምባሳደሯ አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም