የወላይታ ሶዶ ዩኒቨረሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎችና ሠራተኞች የችግኝ ተከላ አካሄዱ

72
ሶዶ ነሀሴ 12/2010 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎችና ሠራተኞች የሃገሪቱን የለውጥ ሂደት በመደገፍ ዛሬ የችግኝ ተከላ አካሄዱ፡፡ ተማሪዎችና ሠራተኞች የችግኝ ተከላውን ያከናወኑት በኮሌጁ ግቢና ኮሌጁ የህክምና መንደር ለመመስረት ባዘጋጀው ቦታ ላይ ነው፡፡ በኮሌጁ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ህሊና አዘዘ በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፈችው ለሃገራዊ ለውጡ ያላትን ድጋፍ ለመግለጽ ነው፡፡ የተከለችው ችግኝ እስኪጸድቅም አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደምታደርግ ገልጻለች፡፡ የችግኝ ተከላው የለውጡን ሂደት ለመደገፍ የተካሄደ ቢሆንም ህክምና ለማግኘት ወደ ህክምና ተቋሙ የሚመጡ ህሙማን የአእምሮ እርካታ እንደሚያገኙ በማድረግ በኩል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጻለች፡፡ ችግኝ መትከል የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል አረንጉዴ ልማት ለመገንባት መንግስት ለያዘው አቅጣጫ ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጤና ባለሙያው አቶ አባተ አረጃ ናቸው፡፡ ''በጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተጀመረውን የመደመር መርህ ከመናገር ባለፈ በተግባር መደገፍ ስላለብን በችግኝ ተከላው ተሳትፌአለሁ'' ብለዋል፡፡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨረሲቲ የማስተማሪያና ሪፌራል ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ሃኪምና የኮሌጁ ዋና ሥራ አስኬያጅ ዶክተር ጌታሁን ሞላ ኮሌጁ ከሃገራዊ ለውጡ ጋር ራሱን ማስኬድ እንዲችል ከተጀመሩ ተግባራት ችግኝ በመትከል አከባቢውን ማሳመር አንዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከ1 ሺህ በላይ አገር በቀል ችግኝ መተከሉን ገልጸው የዉሃ መስመርና ባለሙያ በማሟላት የተተከለው ችግኝ በሙሉ እንዲፀድቅ በትኩረት እንደሚሰራ  ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም