አሸባሪው ህወሃት የአገር አንድነት እሴቶችን በመሸርሸር ኢትዮጵያን ማፍረስ የረጅም ጊዜ እቅዱ አድርጎ ሰርቷል

58

ጥቅምት 19/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያዊ የአንድነት እሴቶችን በመሸርሸር አገር ማፍረስ የረጅም ጊዜ እቅዱ አድርጎ የሰራና እየሰራ ያለ የጥፋት ስብስብ በመሆኑ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ገለጸ፡፡
የአሻባሪው አፈጣጠርና ይዞት የተነሳው ፖሊሲም ጭምር ኢትዮጵያን የመበታተን በመሆኑ የጥፋት ድርጊቱን በመመከትና የአገር ህልውና የማዳን ዘመቻውን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ወንጀለኞችን በአፋጣኝ ለህግ ማቅረብ ይገባል ብሏል።

ወታደራዊው የደርግ ስርዓት መንኮታኮቱን ተከትሎ ህወሃት መንበረ ስልጣኑን በሃይል ከተቆጣጠረ በኋላ በኢትዮጵያውያን ላይ ለማመን የሚከብድ ዘግናኝ ግፍ ፈጽሟል፡፡

ኢትዮጵያውያንን በፖሊሲና በመዋቅር በተደገፈ አሰራር በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል፤ ከአንድነታቸው ይልቅ ልዩነታቸውን በማጉላት የጠበቀ የትብብር እሴታቸውን ለመሸርሸር ብዙ ሰርቷል።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለ27 ዓመታት በበላይነት የዘወረው የህወሃት ቡድን ስብስብ በጥብቅ የሚቃወሙትን በመግደልና በማሰር ዜጎችን በተለያየ መልኩ በመከፋፈል በግጭት ውስጥ የመግዛት ሴራውንም አከናውኗል።

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህርና የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶክተር በቃሉ አጥናፉ እንደሚሉት ህወሃት ወደ ስልጣን ብቅ ያለው የኢትዮጵያን ጠልነት ስሪት ይዞ መሆኑን ይናገራሉ።

ህወሃት በ1967 ዓ.ም ከቀረጸው ማንፌስቶ ጀምሮ በ27 ዓመት የአገዛዝ ዘመኑ ብሎም ባለፉት ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያን አፍርሶ ታሪክ የማድረግ አላማ አንግቦ መሆኑን አብራርተዋል።

የአሸባሪው ህወሃት የፖለቲካ ስሪት ከጥንት እስከ ዛሬ በመከፋፈል የአገር አንድነትን በማሳጣት ኢትዮጵያን የመበታተን እቅድ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን አንድነት በተግባር ለማፍረስ የተመሰረተው ህወሃት አሁን ላይ በአማራና አፋር ክልሎች የሚያደርገው ወረራና አሰቃቂ ጥፋትም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ዶክተር በቃሉ ገለፃ ከሆነ ህወሃት በአማራ በአፋር ህዝብ ላይ የሚያደርሰው ሰቆቃና በደል በኢትዮጵያ ተመልሶ ስልጣን የመያዝ ሳይሆን አገር የማፍረስ ተልእኮውን ለመፈፀም ነው።

በተለይም በአዲሱ መንግስት ላይ ትርምስ በመፍጠር የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ  ትኩረት አግኝቶ በሚጠላት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማብዛት ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አንዳንድ አክራሪ ብሄርተኞች የሚያቀነቅኑት እሳቤም የህወሃት አገር ለማፍረስ እቅድ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያን ድንበር ሲጠብቅ የነበረውን የአገርና የህዝብ መከታ የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ በድንገት ማጥቃቱም "የቡድኑን ማፍያነት" በግልፅ ያሳየ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን አገር ለማፍረስ የተዘጋጀ ካሃዲ ቡድን ለማጥፋት ብቸኛው መፍትሄ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ አጠናቆ በህግ የሚፈለጉትን ለፍትህ  ማቅረብ ይገባል ነው ያሉት ዶክተር በቃሉ፡፡

 አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በርካታ ንጹሃንን በመግደል በሽዎች በማፈናቀል ሃብትና ንብረት መዝረፉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም