ከ6 ሺህ 700 በላይ የፓርኩ ሰራተኞች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ወሰዱ

45

ሀዋሳ፤ጥቅምት 19/2014 ዓ.ም( ኢዜአ) ከ6 ሺህ 700 በላይ ሰራተኞች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት መውሰዳቸውን የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስታወቀ፡፡
የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ከተማ ለኢዜአ እንደገለፁት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከያ መንገዶችን በመተግበር የፓርኩ የዕለት ከእለት ስራ እየተከናወነ ነው።

"በዚህም ፓርኩ ከ30 ሺህ በላይ ሰራተኞችን በመያዝ ስራ ሳይቋረጥ ቀጥሏል"ብለዋል።

ከመከላከያ መንገዶች በተጓዳኝ ሁሉም የፓርኩ ሰራተኞት የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት እንዲወስዱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

እስካሁንም ከ6 ሺህ 700 በላይ ሰራተኞች ክትባቱን እንዲወስዱ መደረጉን አስታውቀዋል።

በቀጣይ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም የፓርኩ ሰራተኞች ክትባት ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ከፓርኩ ሰራተኞች መካከል የኢንቨስተሮች ድጋፍና ክትትል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መንግስቱ ይመር የሥራው ባህሪይና የሰራተኞች ብዛት ፓርኩ ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት ተጋላጭ እንዲሆን ማድረጉን ጠቁመዋል።

ክትባቱን ቀዳሚ ሆነው መከተባቸውን የተናገሩት አቶ መንግስቱ ከዚህ በፊት ስለ ክትባቱ ይነገሩ የነበሩ የተዛቡ አመለካከቶች አሁን ላይ እየቀነሱ መምጣታቸውን አመክተዋል።

ክትባቱ በከፍተኛ ወጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ እንደሆነ ጠቁመው ሁሉም ሰው እድሉን ባገኘበት አጋጣሚ በመከተብ የራሱን፣ የቤተሰቡንና የማህበረሰቡን ህይወት መታደግ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡

በፓርኩ “ የሲልቨር ስፓርክ ” ጨርቃጨርቅና አልባሳት ኩባንያ ሰራተኛ አቶ ሀብታሙ ኤልያስ በበኩላቸው ክትባቱ እንደማንኛውም የክትባት አይነት ከሰውነት ጋር እስኪዋሀድ ከሚፈጥረው እንግዳ ስሜት ባለፈ ምንም አይነት ህመምና ጉዳት እንዳላስከተለባቸው ተናግረዋል፡፡

ሌሎች ባልደረቦቻቸውም ቢሆኑ ከመጠነኛ ራስ ምታት የዘለለ ህመም እንዳላጋጠማቸው ገልፀው ከዚህ በፊት በተሳሳተ ግንዛቤ እምቢተኝነት ያሳዩ ሰራተኞች አሁን ላይ በፈቃደኝነት እየተከተቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡    

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአሁን ወቅት ከ35 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም