የመከነው የምዕራባውያን ከፋፋይ እሳቤ

83

በሚዲያ ሞኒተሪንገና ትንተና

ከ15 ዓመታት በፊት ሦስት የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት አባላት በአንድ ቁልፍ ጉዳይ ላይ ምክክር ይዘዋል። የምክክሩ ማጠንጠኛ ደግሞ ኢራቅን እንደ ቦስኒያ በዘር መከፋፈል ነበር። ከሳዳም ሁሴን ውድቀት በኋላ ለዓመታት ኢራቅ እንደ አገር መረጋጋት ርቋት መታየቷ ለምክክሩ መነሻ ሆኗል። አለመረጋጋቱ በዘመኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንትና ሳዳም ሁሴንን ከመንበረ ሥልጣናቸው አሽንቀጥረው በመጣል ቁልፍ ሚና ለነበራቸው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽም (ትንሹ) እረፍት የነሳቸው ጉዳይ ሆኗል።  

ፕሬዝዳንቱ በኢራቅ ያደረጉትን ጣልቃ ገብነት የጠበቁትን ያህል ስኬታማ አልሆን ሲላቸው ይብከነከኑ ገብተዋል። ይልቁንም ጣልቃ ገብነቱ በህዝባዊ አመጽና ግጭት መታጀቡ ደግሞ የፈላ ዘይት ውስጥ ጣታቸውን የመንከር ያህል እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል። እናም ይህን የኢራቃውያን ህዝባዊ አመጽ ለማብረድ ሲያወጡና ሲያወርዱ ሰነባበተው ሦስት ጉምቱ አሜሪካውያን ሴኔተሮች ጉዳዩን መላ እንዲሉ ሰየሟቸው። እነሱም የወቅቱ ሴናተር የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ ዲ-ዴል እና ሌስሊ ጌልብ ነበሩ።

ሦስቱ ሴናተሮች የኢራቅን ብሔራዊ አንድነት በማስጠበቅ መረጋጋት ያመጣል ያሉትን አማራጭ አቀረቡ። የቀረበው አማራጭም ቦስኒፊኬሽን (Bosnification)የሚል ስያሜን የያዘሲሆን ይህም ቦሲኒያን በዘር የከፋፈሉበት መንገድ ኢራቅ ላይ መተግበርን ዓላማ ያደረገ ነበር።  

ሴናተሮቹ ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት በቦስኒያ የተፈጠረው ክፍፍል ዓይነት በኢራቅ ለመድገም ባግዳድን የፌዴራል መንግሥት ማዕከል እንድትሆን እና ጎሣና ኃይማኖትን መሰረት ባደረገ መልኩ በሦስት ዓበይት የራስ-ገዝ አስተዳደሮች እንድትከፋፈል ተወሰነ። ይህም በበዙት ኢራቃውያን “አገሪቱን ይበታትናል” በሚል ተቃውሞ ገጠመው። በዚህም የአሜሪካ ውጥን ሳይሳካ ቀረ።

“ያዶቆነ ሰይጣን…..” እንዲሉ የያኔው ሴናተር የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ባይደን በኢራቅ ላይ ተሞክሮ የከሸፈው ቦስኒፊኬሸን ኢትዮጵያ ላይ ለመተግበር ደፋ ቀና ማለታቸው ዓለም እየታዘባቸው ይገኛል።

የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ያፈጠጠ ብቻ ሳይሆን የከፋ እንደሆነ ነው የሚነገረው። “እኔ ካልፈቀድኩ አንዴት ተድርጎ…” ዓይነቱ የጣልቃ ገብነት ስላቅ ከኢትዮጵያውያን አልፎ አፍሪካውያንና ሌሎች ሰላም ወደድ አገራትን እያስቆጣ ይገኛል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የሚወጣው መግለጫ አይሉት ዛቻ በግልጽ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በቀጥታ በመግባት የሚፈልጉትን ማሳካት ነው። የባይደን አስተዳደር በአንድ ሉአላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ በመግባት ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡትን መርሆዎች መንካት አትችሉም የሚል ቀጭን ትእዛዝ እስከመስጠት ደርሷል።

በአንድ ሉአላዊ አገር ውስጥ ህገ መንግስት ላይ የመወሰን ስልጣን ያለው ህዝቡና ህዝቡ ብቻ ናቸው። እናም የባይደን አስተዳደር መግለጫዎች ላይ የአገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም የአማራ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ ከትግራይ ክልል እንዲወጡ እንዲሁም የክልል ወሰኖች እና ህገ መንግሥትን አይነኩ የማለት አንድምታው ሉዓላዊነትን ከመዳፈር በላይ ነው።

አሌክስ ሮንዶስ በአፍሪካ ቀንድ የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ልዑክ የነበረ ሲሆን ማርክ ሜዲሽ ደግሞ በዴይተን የሰላም ማስፈጸሚያ ቡድን በኋላም በክሊንተን አስተዳደር ውስጥ በአሜሪካ ግምጃ ቤትና ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት አገልግሏል። አሌክስ ሮንዶስ እና ማርክ ሜዲሽ ኢትዮጵያን አስመልክቶ የፃፉት ትንታኔ በኢትዮጰያ ላይ የተቃጣ ጣልቃ ገብነትና ከፋፋይ ሴራ ስለመኖሩ ማሳያ ነው።

“Ethiopia Is Plunging into Chaos. It’s Time for A New Dayton Peace Process”በሚል ርዕስ በእነዚህ ግለሰቦች ለንባብ የበቃው ትንታኔ ለማመን ቢከብድም ኢትዮጵያን ቅርጫ ለማድረግ ሴራ እየተጎነጎነ መሆኑን ፍንትው አርጎ አሳይቷል።

የዴይተን ስምምነት (Dayton Accord)በቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና መካከል የተደረሰ አጠቃላይ የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ ነው። ስምምነቱ እኤአ በ1995 በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት ዳይተን አቅራቢያ በሚገኘው የራይት ፓተርሰን አየር ሃይል ማዘዣ የተደረሰ ስምምነት ሲሆን የዩጎዝላቪያ መበታተንን ተከትሎ የተፈጠረው የቦስኒያ ጦርነት ለማስቆም ያለመ ነበር። በተጨባጭ የሆነው ግን አንድ ሉዓላዊ አገር የነበረችውን ቦስኒያ-ሄርዞጎቪናን ሁለት አገር ሆና እንድትከፈል ነው።

የፖለቲካ ተንታኙ አንድሪው ካሪብኮ “The U.S. Wants to Turn Ethiopia into Bosnia”በሚል ርዕስ ባስነበቡት ትንታኔ የባይደን አስተዳደር ከማዕቀብ እስከ መልከ-ብዙ ጦርነት ኢትዮጵያ ላይ በመክፈት ዩጎዝላቪያ ያጋጠማትን የመበታተን ዕጣ ለመድገም እየሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል። በብዙ መልኩ ስኬታማ እንዳልሆነ የሚነገርለት የዴይተን ስምምነትን ለኢትዮጵያ “ይበጃል” በሚል አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ቦስኒፊኬሽንን ገቢራዊ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው የሚያረጋግጥ መሆኑን ነው አንድሪው ካሪብኮ የሚያስረዱት።       

ተንታኙ እንደሚገልጹት አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በመደገፍ ትግራይን ጨምሮ ክልሎች ሰፊ የራስ-ገዝ አስተዳደር እንዲኖራቸው በማድረግ ደካማ ማዕከላዊ መንግሥት መፍጠር ብሎም የኢትዮጵያ አንድነትን ማላላት ምእራባውያን የያዙት የቦስኒፊኬሽኑ ግብ ነው።

አሜሪካ ኢራቅን በመውረር ከቻለች አገሪቷን መከፋፈል ካልሆነም ደካማ የአሸንጉሊት መንግሥት ለመመስረት ጥረት አድርጋለች። ክፍፍሉ ባይሳካለትም በኢራቅ ተላላኪ መንግሥት መመስረት ችላለች። ይህን ግን ኢትዮጵያ ላይ ማድረግ አይቻላትም ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ። ከቦስኒፊኬሽን ጀርባ የተዶለተው ኢትዮጵያን የመበታተን ሴራ ኢትዮጵያውያን በውል ተገንዝበው አገራዊ አንድነታቸውን ማጠናከራቸው በምክንያትነት ያስቀምጣሉ። ይህ ደግሞ  ምዕራባውያን ማስታገሻ ያጡለት ራስ ምታት ሆኗል።    

በአሜሪካ አጋሮች የሚጎሰሙ የፕሮፖጋንዳ ነጋሪቶችም የቦስኒፊኬሽን ጨለምተኛ ሀሳብ የተጣባቸው ስለመሆናቸው የሚያወጧቸው ዘገባዎች ማሳያ ናቸው። የእንግሊዝ ፓርላማ አባል የሆኑት አርሚንካ ሄሊች “In Ethiopia, Echoes of Yugoslavia ሲሉ ያስነበቡት ትንታኔም “ሊበሏት ያሰቧት አሞራ……” እንዲሉ ለዓላማቸው ማሳኪያ ሰንካለ ምክንያት መሆኗ ነው።

ይህን እሳቤን በመደገፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አገራት ጣልቃ ለመግባት የሚያሴሩ ምእራባውያን ከመከነው የኢራቅ ቦስኒፊኬሽን ትምህርት ሊወስዱ ይገባል። ዩጎዝላቪያን በታትኖ ኢራቅን ለድቀት የዳረገው የባይደን-ጌልብ የቦሲኒፊኬሽን እሳቤ ኢትዮጵያ ላይ ለመተግበር መሞከር አንድም ከስህተት አለመማር አሊያም የኢትዮጵያውያን ስነ-ልቦና በውል አለመገንዘብ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ዩጎዝላቪያ ወይም ኢራቅ አይደለችምና!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም