ድርጅቱ ለጥበበ-ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 29 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ለገሰ

54

ባህር ዳር ፤ጥቅምት 18/2014 (ኢዜአ) ሲዊዲን ሀገር የሚገኝ "ሂውማን ብሪጅ" የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ለባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ-ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 29 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሶች ዛሬ ለገሰ።
 የሕክምና ቁሶቹ  ሆስፒታሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እያደረገ ያለውን ሥራ እንደሚያግዝ የድርጅቱ  ሥራ አስኪያጅ የክብር ዶክተር አዳሙ አንላይ በርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ገልጸዋል።

በድጋፉ  ለምርመርና ለሕክምና የሚያገለግሉ ግብአቶች እንዲሁም  የእጅ ንጽህና መጠበቂያና አልኮል መካተታቸውን ጠቅሰዋል።

ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ ድጋፉ ለመተጋገዝ የተደረገ ሲሆን አጠቃላይ ወጪውም 29 ሚሊዮን ብር የሚገመት ነው።

እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የዜግነት ድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን አመለክተው፤ ድጋፉ እንዲደረግ ፍቃደኛ ለሆኑ የውጭ ዜጎችም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያን የሕክምና ተቋማት አቅም ለማጎልበት ድርጅቱ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ-ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቀጣይ ለሚያከናውናቸው የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችም ድርጅቱ ድጋፉን እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።

ሂውማን ብሪጅ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ከዚህ ቀደም ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የገለፁት ደግሞ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር የሺጌታ ገላው ናቸው።

የተደረገው ድጋፍ ለሆስፒታሉ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ድጋፉ ለጥበበ-ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ ሳይሆን በዙሪያው በትብብር ለሚሰሩ የጤና ተቋማትም እንደሚተርፍ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ላደረገው የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ፕሮፌሰሩ፤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ በቀጣይ ለሚያስገነባው ማስፋፊያ ድርጅቱ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።  

"በማስፋፊያ ስራው 1ቢሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ግብዓት ለማቅረብ ከሂውማን ብሪጅ ጋር የስምምነት ፊርማ ተፈራርመናል" ሲሉም አክለዋል።

በድጋፍ ርክክቡ  ወቅት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና የተለያዩ የዲያስፖራ አባላት ተገኝተዋል ሲል ከሥፍራው የዘገበው የኢዜአ ሪፖርተር  ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም