ህብረተሰቡ የህግ የበላይንትን በጠበቀ መልኩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአስተሳሰብ ደረጃ ታግሎ ማሸነፍ እንደሚገባው አስተያየት ሰጭዎች ተናገሩ

68
ነሃሴ 12/2010 ህብረተሰቡ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአስተሳሰብ ደረጃ ታግሎ ማሸነፍ እንጂ የህግ የበላይንትን አደጋ ውስጥ በሚጥል መልኩ መሆን እንደሌለበት በአዲስ አበባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በሀገሪቱ የሰላም የእርቅና የአንድነት አስተሳሰብን ባልተገባ መልኩ በመተርጎም የሰው ሂወት ማጥፋት፣ ንብረት መዝረፍና ማቃጠልና የእምነት ተቋማትን ማቃጠል ጨምሮ በርካታ ህገወጥ ድርጊቶች በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲፈጸሙ እየተስተዋለ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ፍትህ ቢሮ አቃቤ ህግ አቶ ስራውብዙ ወልዴ እንዳሉት ባለፉት አራት ወራት በሀገሪቱ የመጣው የአስተሳሰብ ለውጥ ይበልጥ እኩልነትንና አንድነትን የሚያጠናክር  በመሆኑ  የህግ የበላይነትን ማስከበር ከሁሉም ይጠበቃል፡፡ መደመር ማለት መቀነስ ሳይሆን ህብረተሰቡ በማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና በፖለቲካ ዘርፎች የሚፈልጋቸውን መብቶች በጋራ ተባብሮ እንዲያረጋግጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ህዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ በዘመናዊ መልኩ መግለጽ የሚፈልገውን ሃሳብ ገልጾ ለመመለስ  በሚያደርገው ሂደት ወደአላስፈላጊ ጥፋት የሚያስገቡ አጋጣሚዎች እየታዩ መሆናቸውን ነው አቃቤ ህጉ የተናገሩት፡፡ በስሜታዊነት በመገፋፋት ወደጥፋት በመግባት የህግን የበላይነት አለመቀበል ለውጡን የማይደግፉ አስተሳሰቦች ምክንያት ሊሆኑ ስለሚችሉ  ህብረተሰቡ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በአስተሳሰብ ደረጃ ታግሎ ማሸነፍ እንጂ ህግን በመጣስ መሆን እንደሌለበት አቶ ስራውብዙ ገልጸዋል፡፡ አሁን የሚስተዋሉ ችግሮች የወጣቱ ሳይሆኑ ለውጥን የሚጻረሩ ሃይሎች በመሆኑ ወጣቱ የለውጥ ሀይልና የቴክኖሎጂ ፈጠሪ እንጂ ስርአት አልበኝነት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ላይ የሚሳተፍ  መሆን እንደሌለበት ገልጸዋል፡፤ "ህግ ማለት የህዝብ አይን ነው፤ ህዝብ ማንኛውንም አካል ሲያጠፋም ሆን ሲያለማ ያያል "ያሉት አቶ ስራውብዙ ይህም መንግስት ወደሙሉ ህግ ማስከበር ሲገባ ችግር የፈጠረ ተጠያቂ መሆኑ የማይቀር መሆኑን አስረድተዋል ፡፡ ህግ አስከባሪው አካል የፈለገውን እርምጃ ቢወስድ በህዝብ ተቀባይነት ከሌለው  የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም ያሉት አቃቤ ህጉ የህግ የበላይነት እንዲከበር በዋናነት ህዝቡ ዘብ መቆም እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡ መግስትም ለውጡን የሚያጠናክሩ  ተቋማዊ አደረጃጀቶችን እስከ ታች ድረስ በማውረድ መስራት ካልተቻለ ከለውጡ ተቃራኒ ሃይሎች ጋር የሚጋጭበት ሁኔታ  መፈጠሩ አይቀም ነው ያሉት፡፡ አሁን የተገኘውን ለውጥ ለሕዝብ ተጠቃሚነትና ለሀገር እድገት በማዋል የህግ የበላይነትና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ አቶ ፉአድ ሽኩር የተባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ በበኩላቸው አሁን ላይ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በስሜታዊነት በመንቀሳቀስ ህግን የሚቃረኑ ተግባራት ሲፈጸሙ እንደሚታይና የህብረተሰቡን ሰላም ለአደጋ እያጋለጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የተገኘውን ነጻነት ለማጠናከር ህብረተሰቡ ከህግ አስከባሪዎች ጋር በመተባበር የህግ  የበላይነትን  ማስከበር የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ የህግ የበላይነት አለመከበር የሀገር ህልውና አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል ያሉት ደግሞ  አቶ ደረጄ ሀይሌ የተባሉ የመዲናዋ ነዋሪ ናቸው፡፡ ወጣቱ በተረጋጋ ሁኔታ ማንኛውንም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በህግ አግባብ ፍትህ እንዲያገኙ ወደ ህግ አስከባሪ አካላት ማድረስና ማሳወቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም