"በቅን አሳቢ ለጋሾች የዓይን ብርሃኔ ተመልሷል"

64

ጥቅምት 18/2014 በምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ከተማ ተወልዶ ያደገው ወጣት ፍሬው ሺበሺ"በቅን አሳቢ ለጋሾች የዓይን ብርሃኔ ተመልሷል"ይላል፡፡

በአካባቢው በሚገኘው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት በ "አውቶ-መካኒክስ" ዘርፍ ስልጠና በመውሰድ በሞተረኝነት የስራ መስክ ተሰማርቶ ህይወቱን ሲመራ ቆይቷል፡፡

ወጣት ፍሬው ከአስር ዓመታት በፊት ጀምሮ የግራ ዓይኑ ጠባሳ እይታው እየቀነሰ መጣ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜም ችግሩ እየተባባሰ እንደሄደበት ይናገራል፡፡

ከእይታ መቀነስ ጋር ተያይዞ ስራውን እንደፈለገ ተንቀሳቅሶ መስራት አለመቻሉ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አስከፊ አደረገው፡፡

ወጣት ፍሬው በወቅቱ በአካባቢው በሚገኙ የጤና ተቋማት ለህክምና ቢሄድም ብርሃኑን መመለስ የሚያስችል መፍትሄ እንዳላገኘ ይገልጻል፡፡

ሁኔታው እየተባባሰ ሲመጣም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ህክምና መከታተል የጀመረ ሲሆን፤ የግራ ዐይኑ ዳግም ብርሃን የማየት እድል የሚያገኘው በዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ብቻ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡

ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ በሚኒሊክ ሆስፒታል ወረፋ በመያዝ ለዓይን ባንክ የዐይን ብሌን የሚለግሱ ቅን ልቦችን መጠባበቅ  ነበረበት፡፡

ለሶሰት ወራት ወረፋ ከጠበቀ በኋላም የዓይን ብሌናቸውን በለገሱ ቅን አሳቢዎች አማካኝነት ውጥኑ ተሳክቶ የግራ ዓይኑ ዳግም ብርሃን ማየት እንደቻለ ገልጿል፡፡

"ንቅለ ተከላው በተሳካ ሁኔታ ተከናውኖ ብርሀን ማየት የጀመርኩበት ቀን ላይ የተሰማኝን ስሜት ለመግለፅ ቃላት ነው ያጠረኝ" ሲል በውቅቱ የተሰማውን ስሜት ይናገራል ፡

ከሶስት ዓመታት በፊት በደረሰባት የአሲድ ጥቃት የቀኝ ዓይኗን እይታ እንዳጣች የምትናገረው ደግሞ ወጣት ሜላት ተሰማ ናት፡፡

ካጋጠማት ጉዳት ጋር የሚጣጣም የዓይን ብሌን ባለመገኘቷ ምክንያት ላለፉት ሶስት ዓመታት ወረፋ እንድትጠብቅ መገደዷን ትናገራለች፡፡

በኢትዮጵያ የዓይን ብሌን የመለገስ ባህል አናሳ መሆኑ በቶሎ መፍትሔ እንዳታገኝ ማድረጉን የምትናገረው ወጣት ሜላት፤ ይህም ከደረሰባት ጥቃት ጋር ተደምሮ ለከፋ የስነ-ልቦና ጫና አጋልጧት መቆየቱን አንስታለች፡፡

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ዓይን ባንክ አማካኝነት ለእርሷ የሚሆን የዓይን ብሌን እንደተገኘላትና በቅርቡ የዓይን ንቅለ ተከላ እንደምታደርግም ገልጻልናለች፡፡

ከንቅላ ተከላው በኋላም እንደፈለገች ተንቀሳቅሳ ልጇን ለማሳደግ ተስፋ ሰንቃለች፡፡

የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ ዳይሬክተር ወይዘሮ ለምለም አየለ ባንኩ ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች የሚያገኛቸውን የዐይን ብሌኖች ለጤና ተቋማት በማሰራጨት የዓይን ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ዳግም ብርሃን እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የዓይን ብሌን የመለገስ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን በሚለከት በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንዳልተከናወኑ ጠቅሰው፤ ባንኩ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እይታቸው በቀላሉ መመለስ እየቻለ  በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ለመታደግ የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የሚገቡ በጎ ፈቃደኞች መበራከት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዐይን ባንክ ከተመሰረተ 18 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ እስካሁን ባለው ሂደትም 2 ሺህ 670 ሰዎች የዓይን ብሌን አግኝተው እይታቸው እንዲመለስ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም