በክልሉ በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል

95

አሶሳ ፤ ጥቅምት 18/ 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 53 በመቶ መቀነሱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የጸረ ወባ በሽታ ንቅናቄ ሳምንት ዘመቻ በባምባሲ ከተማ በተጀመረበት ወቅት  የክልሉ ጤና ቢሮ  ሃላፊ አቶ ፈቃዱ ረጋሳ   እንዳሉት፤ በክልሉ እንደአውሮፓ አቆጣጠር በ2015 በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 249ሺህ 156 ነበር።

ይህ ቁጥር ከአምስት ዓመት በኋላ ወደ 181ሺህ 454 ዝቅ ማለቱን አመልክተዋል።

በእነዚህ ዓመታት በበሽታው ህይወታቸው ያልፍ የነበሩ ሰዎች ብዛት ከ34 ወደ 16 መውረዱን ጠቅሰው፤ በዚህም በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ53 በመቶ መቀነሱን ነው ያስታወቁት፡፡

ወባ በክልሉ  በእነዚህ ዓመታት በወረርሽኝ መልክ እንዳልተከሰተም ገልጸዋል።

የአጎበር ስርጭት፣ የአካባቢ ጽዳት፣ የመድሃኒት ስርጭት፣ የምርመራ እና የመድሃኒት አቅርቦት ስራዎችን ለማጠናከር የተደረገው ጥረት ውጤት እንዲገኝ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

"ይሁንና የበሽታውን ስርጭት ለማስቆም በተከናወኑ ተግባራት ልክ ውጤት ባለመመዝገቡ በቀጣይ የተጠናከረ ሥራ መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።

በቀጣይ አስር ዓመት ወባን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ለተያዘው ዕቅድ ስኬት የክልሉን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት በማድረግ ወባን ለመከላከል የሚያስችሉ አቅጣጫዎች በጥናት እየተለዩ መሆኑንም አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል።

በጤና ቢሮው የወባ በሽታ ማስወገድ ባለሙያ ወይዘሮ ንጹህ ታደሰ በበኩላቸው ወባን ለመከላከል በነጻ የሚታደሉ የአልጋ አጎበሮች ከግንዛቤ ማነስና ከግዴለሽነት ለሌላ አገልግሎት እየዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ የጸረ-ወባ ኬሚካል የተረጩ ቤቶችን ሲለስንና ቀለም ሲቀባ የሚስተዋልበት ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል፡፡

እንደባለሙያዋ ገለጻ ፤ ለመንገድ ሥራ እና ለባህላዊ ወርቅ ማምረት የሚቆፈሩ ጉድጓዶች መልሰው አለመደፈናቸው የወባ በሽታን ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት በሚፈለገው መንገድ እንዳይሄድ አድርጓል።

"የወባ በሽታን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ከማስፈለጉ ባለፈ የህብተሰቡን ግንዛቤ ይበልጥ ማሳደግ ላይ በትኩረት መስራት ይገባል" ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ አመራሩ ግንባር ቀደም ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

እስከ ጥቅምት 23 / 2014ዓ.ም በሚቀጥለው የንቅናቄው ሳምንት ነጻ የወባ ምርመራ፣ የአካባቢ ጽዳት እና ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም