የፀረ-ሽብር አዋጁ የፍትህ ሰርዓቱና የተቋማትን ገለልተኝነት ባስጠበቀ መንገድ ሊሻሻል ይገባል-የውይይት ተሳታፊዎች

60
አዲስ አበባ ነሃሴ12/2010 የፀረ ሽብር አዋጁ የፍትህ ስርዓቱና የተቋማትን ገለልተኝነት በሚያስጠብቅ መልኩ መሻሻል እንዳለበት ተገለፀ። በኢትዮጵያ በስራ ላይ የሚገኙ ሕጎችን ለማሻሻል በቅርቡ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የተቋቋመው የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ምክር ቤት በፀረ- ሽብርና በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጆች ላይ ባካሄደው ጥናት ላይ ዛሬ ምክክር ተደርጓል። የፀረ-ሽብር አዋጁን ለማሻሻል ስራውን የጀመረው አጥኝ ቡድኑ ባቀረበው ጥናትም፤ የሽብርተኝነት ጽንሰ ሃሳብ፣ የኢትዮጵያ ፀረ-ሽብር አዋጅ አተገባብርና ታሪካዊ አመጣጥ፣ መሰረታዊ የወንጀል ስነ ስርዓት መርሆች፣ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችና የመፍትሔ ሀሳቦች በዝርዝር ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በ2001 ዓ.ም የወጣው ፀረ-ሽብር አዋጁ በዓረብ ፀደይ አብዮት፣ በድምጻችን ይሰማ፣ በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃዉሞ ጉዳይ እንዲሁም ከቅርብ ዓመታት ህዝባዊ ተቃውሞዎች በፍርድ ቤት ጉዳያቸው በተያዙ ተጠርጣሪዎችና ተከሳሾች ላይ በብዛት ተግባራዊ ሲሆን መቆየቱ ተገልጿል። ከሽብር ተጠርጣሪዎች መካከልም 1 ሺህ 128 በኦነግ፣ 648 ተጠርጣሪዎች ደግሞ በአርበኞች ግንቦት ሰባት አባልነትና ግብረ አበርነት ፍርድ ቤት መቅረባቸው በአዋጁ ታሪክና አተገባበር ጥናቱ ተመልክቷል። አዋጁ ከምርጫ 97 በኋላ ገዢው ፓርቲ "ስልጣኑን ለማራዘም ለፖለቲካ ፍጆታ ያወጣው፤ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ያጠበበ አፋኝ ሕግ እንጂ በወቅቱ አገሪቷን ሽብር ስጋት ላይ የጣለ ጉዳይ እንዳልነበር" በመድረኩ ላይ ተገልጿል። የአዋጁ መሰረታዊ ጉዳዮች፣ በወንጀል ስነ ስርዓት ሕግና የማስረጃ ጉዳዮች፣ በሽብርተኝነት አተገባበር ኮሚቴ በተጠቀሱ አንቀጾችም ሰፊ የአተገባበርና ትርጉም ክፍተቶች የተስተዋለበት ነው ተብሏል። በአዋጁ አንቀጽ 3፣ አንቀጽ 6፣ አንቀጽ 10፣ አንቀጽ 19፣ አንቀጽ 20፣ አንቀጽ 25 የተጠቀሱ ጉዳዮች ለአብነት መሻሻልና ዝርዝር ትርጉም ከሚያስፈልጋቸው ድንጋጌዎች መካከል ተጠቅሰዋል። ያም ሆኖ የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል ፀረ-ሽብር አዋጁ 'መሻር ወይስ መሻሻል' በሚሉ ጭብጦችን ያነሳው ጥናቱ የሽብርተኝነትን ዓለም አቀፋዊነትና የአፍሪካ ኮንቬንሽን፣ ኢትዮጵያ የምትገኝበት አህጉራዊ ቀጠና፣ የወንጀል ሕጉ ሁሉንም አይነት ወንጀሎች ለመመለስ ብቁ አለመሆን፣ የጸጥታው ምክር ቤት ሪፖርትና ሌሎች ምክንያቶች ህጉ እንዲሻሻል ጥቆማዎችን ሰጥቷል። የፀረ ሽብር ሕጉ መሻር እንዳለበት የገለጹ ተሳታፊዎች እንዳሉ ሁሉ፣ በየትኛውም አገር ሕጎች እንደሚወጡ የሚገልጹት አብዛኛው ተሳታፊዎች ግን የፀረ ሽብር አዋጁ የፍትህ ስርዓቱና ተቋማት ገለልተኝነት በሚያስጠብቅ መልኩ መሻሻል እንዳለበት ገልጸዋል። በተለይም በሽብር ጥቃት የደረሰባቸው ወገኖች ካሳ እንደሚያስፈልግ ሁሉ፤ የፀረ-ሽብር አዋጁና በፍትህ ስርዓቱ መጓደል ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ካሳ ጉዳይ ታሳቢ መደረግ እንዳለበት ነው የተገለጸው። በአዋጁ አተገባበር በኩል ማስረጃ ለማሰባሰብ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በጎደለው መልኩ በፍትህ ተቋማት የሚፈጸሙ ኢ -ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮች ድርጊቶችን በሚያስወግድ መልኩ መሻሻል እንዳለበትም በምክክር መድረኩ ተነስቷል። የፀረ-ሽብር ሕጉን ለማሻሻል ግብዓቶችን ለማሰባሰብ አማካሪ ምክር ቤቱ ተጨማሪ መድረኮችን ያካሄዳል ተብሎም ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም