ዓመታዊው የጤና ዘርፍ የምክክር ጉባኤ በጂግጂጋ ከተማ ይካሄዳል

57

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)  23ኛው ዓመታዊ የጤና ዘርፍ የምክክር ጉባኤ ከፊታችን አርብ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በጂግጂጋ ከተማ የሚካሄድ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ጉባኤው “ ምላሽ ሰጪ የጤና ስርዓት በአዲስ ምዕራፍ " በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 19 እስከ 21 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ተገልፇል፡፡

የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ፤ በጉባኤው የጤና ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች፣ የሁሉም ክልል የጤና ቢሮ ሃላፊዎች፣ አጋር አካላት እና የተጠሪ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ይሳተፋሉ።

በጉባኤው መጀመሪያው ቀን ማለትም ጥቅምት 19 በጂግጂጋና አካባቢው የመስክ ጉብኝት የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ሞዴል የሆኑ የቤተሰብ ቤት እና ሞዴል የጤና ተቋማት የሚጎበኙ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ደግሞ መደበኛ ጉባኤው ይካሄዳል ብለዋል።

በጉባኤው 400 ሰዎች የሚሳተፉ መሆኑን ጠቁመው የኮቪድ 19 ፕሮቶኮል መመሪያዎች በተጠበቀ መልኩ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

በጉባኤውም የ2013 ዓ.ም የጤናው ዘርፍ አፈጻጸም የሚዳሰስ መሆኑን ጠቁመው በ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት የሚካሄድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በጤናው ሴክተር በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተያዙ ዋና ዋና ግቦችን በጋራ ለማሳካትም የመግባቢያ ሰነድ የሚፈረም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጉባኤው በስራ አፈጻጸማቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ የጤና ባለሙያዎች እውቅና የሚያገኙ መሆኑም ጠቁመዋል።

ከሁሉም ክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተመረጡ የጤና ባለሙያዎች በአገር አቀፍ ደረጃ በወጣው መስፈርት መሰረት ተወዳድረው ለአሸናፊዎች እውቅና ይሰጣል ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ ለየት ያሉ ግኝቶችን የፈጠሩ ተመራማሪዎችም የሚሸለሙ መሆኑንም ዶክተር ተገኔ ጠቅሰዋል።  

22ኛው ዓመታዊ የጤና ዘርፍ የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም