በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚመዘገበው ሞት 6 ነጥብ 23 በመቶ በስትሮክ ሳቢያ ነው

72

ጥቅምት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚመዘገበው አጠቃላይ ሞት 6 ነጥብ 23 በመቶ የሚሆነው በስትሮክ ህመም ሳቢያ ነው።

የስትሮክ ሳምንት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፊታችን አርብ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ይከበራል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደገለጹት፤ ስትሮክ በዓለም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ገዳይ ከሚባሉ በሽታዎች ተርታ የሚጠቀስ ነው።

"በዓለም ላይ በየአመቱ 13 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች በስትሮክ በሽታ እንደሚጠቁ ጠቅሰው፤ በየአመቱ ከ5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህይወታቸውን በዚሁ በሽታ ሳቢያ ያጣሉ" ብለዋል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚመዘገበው አጠቃላይ የሞት ምጣኔ መካከል 6 ነጥብ 23 በመቶው በስትሮክ ሳቢያ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ሕብረተሰቡ ስለ በሽታው ሰፊ ግንዛቤ ኖሮት ራሱን መከላከል እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

የህክምና ባለሙያዎች ስለ በሽታው አስከፊነትና ገዳይነት ለህብረተሰቡ ማሳወቅና የመከላከያ መንገዶችን ማሳወቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኒዩሮሎጂስቶች ማህበር ጸሐፊ ዶክተር ሜሮን አውራሪስ ስትሮክ በአንጎላችን ክፍል ውስጥ ያለው የደም ዝውውር በተለያዩ ምክንያቶች በድንገት መቋረጥ ምክንያት የሚከሰት በሽታ መሆኑን አብራርተዋል።

ሁለት ዓይነት የስትሮክ ህመም አይነቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ዶክተር ሜሮን፤ በህክምናው አጠራር "ኢስኬሚክ እና ሄሞራጂክ" እንደሚባሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም የስትሮክን በሽታ ለመከላከል ማህበረሰቡ ከተላላፊ በሽታዎች ራሱን መጠበቅ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለአንድ ሣምንት በሚከበረው የስትሮክ ሳምንት ህብረተሰቡ ስለ በሽታው አስከፊነት ተረድቶ ራሱን እንዲከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በስፋት መከናወን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በአለም ላይ በስትሮክ በሽታ በአማካይ በየአራት ደቂቃው 1 ሰው እንደሚሞት ጥናቶች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም