በጋምቤላ ክልል ከ379 ሺህ በላይ ህዝብ ከወባ በሽታው መከላከል ተቻለ

78

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 17/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በተካሄደ የፀረ- ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ከ379 ሺህ በላይ ህዝብ ከበሽታው መከላከል መቻሉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

‘‘ወባን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል’’ መሪ ሐሰብ  ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የአካባቢ ጽዳትና ቁጥጥር ዘመቻ ዛሬ በክልሉ በይፋ ተጀምሯል።

ዘመቻው ሲጀመር የቢሮው ኃላፊ አቶ ሮት ጋትዊች እንዳሉት፤ በወባ በሽታ ተጋላጭነት የጋምቤላ ክልል ቀዳሚ ነው።

ባለፈው የክረምት ወቅት በክልሉ ከ514 ሺህ በላይ ህዝብ ለወባ በሽታ የመጋለጥ ሁኔታዎች እንደነበሩም ጠቅሰዋል።

በክልሉ ያለውን የወባ ተጋላጭነት ታሳቢ በማድረግ በክረምቱ መግቢያ በሁሉም ወረዳዎች በ117 ሺህ 564 ቤቶች ላይ በተካሄደ የፀረ- ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት 379 ሺህ 688 ሰዎችን ከበሽታው መከላከል መቻሉን አስታውቀዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት  በ138 ሺህ 269 ሰዎች ላይ በተካሄደ የደም ናሙና ምርመራ 56 ሺህ 416 ሰዎች በበሽታው ተይዘው መገኘታቸውን አስታውሰዋል።

ይህም የሚያሳየው ለመከላከል እየተከናወኑ ባሉት ስራዎች በሽታው የመቀነስ አዝማሚያ እየታየ ቢሆንም   የስርጭት መጠን አሁንም ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል።

ህብረተሰቡ አካባቢውን በማጽዳት፣ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስ፣ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር በአግባቡ በመጠቀም በሽታውን ለመከላከል ጥረት ማድረግ እንደለበት አሳስበዋል።

ወባን የመከላከል ሳምንታዊ የጽዳትና ቁጥጥር  ዘመቻ በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎችን  ለማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ እንደ ሀገር የወባ በሽታን ለማጥፋት የተያዘውን እቅድ በክልሉም ገቢራዊ ለማድረግ ህብረተሰቡ አጎበር በመጠቀምና የአካባቢውን ጽዳት በመጠበቅ  የድርሻውን እንዲወጣ ያመለከቱት ደግሞ የጤና ቢሮው የበሽታ መከላከልና ጤና ማበልጸግ ዳይሬክተር  አቶ ዊው ጋች ናቸው።

ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ዘመቻ የአካባቢ በሁሉም ወረዳዎች አካባቢን የማጽዳት፣ ውሃ የቋጠሩ ቦታዎች የማፋሰስና ሌሎች  ስራዎችም እንደሚከናወኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም