ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ዓላማ ስኬት ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ያስፈልጋል

68

ጥቅምት 17 / 2014 (ኢዜአ) የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ዓላማ ለማሳካት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ እንደሚያስፈልግ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ ገለጹ።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ኤክስቴንሽያ በተባለ ኩባንያ ትብብር የተዘጋጀው 18ኛው የዲጂታል አፍሪካ ኢኖቬሽን ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በኢትዮጵያ ለ5ኛ ጊዜ እየተካሄ ባለው ጉባኤ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችና የሞባይል ኔትወርክ ኦፕሬተሮች ተሳትፈዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ ሞላ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳው ኢትዮጵያን በ2030 ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር መሸጋገርን ኢላማ ያደረገ ነው።

በዚህም አገሪቱ የበለፀገች መካከለኛ ገቢ ያላት አገር እንደምትሆን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት የሚያስችሉ የሕግ፣ የፖሊሲና የማዕቀፍ ማሻሻያዎችን እያደረገች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

መንግስት ዘርፉን በዲጂታል መልኩ መለወጥ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ለአብነትም የቴሌኮም ዘርፉን አንስተዋል።

የኤክስቴንሽያ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ታሪቅ ማሊክ በበኩላቸው በጉባኤው ከ47 አገራት የተውጣጡ 250 ድርጅቶች መሳተፋቸውንና ከእነዚህም 171 የግል ኩባንያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የሚደገፉና የሚበረታቱ መሆናቸውን አንስተው፤ ድርጅታቸው በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሚሰሩ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰሩ እንደሚመክር ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የስራ ተነሳሽነት ያላቸው በርካታ ወጣቶች አሏት ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህን አቅም በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

"የዘንድሮው ጉባኤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ውሳኔዎችን ባሳለፈችበት ወቅት መሆኑ ለየት ያደርገዋል" ያሉት ደግሞ የሚኒስቴሩ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዮት ባዩ ናቸው።

ጉባኤው የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተሞክሮ የሚቀስሙበት እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም