የኢትዮጵያዊያንን ሰቆቃ ከሚያስቀሩ ፕሮጀክቶች አንደኛው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ነው

59

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 17/2014 (ኢዜአ) ''የኢትዮጵያዊያንን ሰቆቃ ከሚያስቆሙ ፕሮጀክቶች አንዱ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ በመሆኑ ለስኬቱ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል'' ሲሉ ኡስታዝ ጀማል በሽር ይናገራሉ።

ኡስታዝ ጀማል በአጭር ጊዜ ለግድቡ ግንባታ የሚውል 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ችለዋል።

የኢትዮጵያ የሠላምና የዕድገት ማዕከል ምክትል ሊቀመንበርና የ"ኪንግስ ኦፍ አባይ" ሚዲያ ፕሬዝዳንት ኡስታዝ ጀማል በሽር ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

'ኪንግስ ኦፍ አባይ' ሚዲያ በዓረብኛ ቋንቋ በግብጽ በኩል ግድቡን አስመልከቶ የሚቀርቡ መረጃዎችን ወደ አማርኛ በመተርጎም ለኢትዮጵዊያን ያቀርባል።

ይህም ብቻ አይደለም የኢትዮጵያን እውነታም በዓረብኛ ቋንቋ በመተርጎም የዓረቡ ዓለም ማኅበረሰብ  ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛል።

"ኢትዮጵያዊያን ካለንበት የድህነት ሰቆቃ የምንወጣው የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ስንጨርስ ነው" የሚሉት ኡስታዝ ጀማል ግድቡ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ሌሎች ችግሮችን ማለፊያ መንገድ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።

እውነታው ይህ በመሆኑ ግብፅም ሆነች ሌሎች የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አካላትን መታገል ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ይህ ደግሞ በተለየ መንገድ ሳይሆን ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ ማንንም ሳትጎዳ በፍትሃዊነት የምትጠቀም አገር መሆኗን በማሳወቅ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በርካታ  ኢትዮጵያዊያን በወጣትነት ዕድሜያቸው በስደት ለተለያዩ ችግሮች የሚዳረጉት በድህነት ምክንያት መሆኑ መረሳት የለበትም ብለዋል ኡስታዝ ጀማል በሽር።

ለኢትዮጵያዊያን በርካታ ጥቅሞችን ይዞ የሚመጣው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ጥረት ማድረግ አለበት ባይ ናቸው ኡስታዝ ጀማል።

እርሳቸው በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን እና የተለያዩ አገራት ዜጎችን በማስተባበር 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማሰባሰባቸውንም ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት ኢትዮጵያዊያን ያለ ምንም ልዩነት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሕዳሴ ግድብ በሚችለው አቅሙ መንቀሳቀስ እንዳለበትም አመልክተዋል።

የሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ ያነሱት ኡስታዝ ጀማል የኢትዮጵያዊያንና የሱዳን ሕዝቦች የቆየ ወዳጅነት ያላቸው በመሆኑ ለአገሪቱ ሠላምና መረጋጋት የኢትዮጵያ መንግስት የበኩሉን ቢያደርግ መልካም መሆኑን ገልጸዋል።

ኡስታዝ ጀማል በሽር የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሳወቅ 

ይታወቃሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም