በኢትዮጵያ የሚገነባው የመጀመሪያው የቴክኖሎጂ ከተማ የአገሪቷን ታሪክ መሰረት ያደረገ እንደሆነ ተገለጸ

185
አዲስ አበባ ነሀሴ 12/2010 አማራ ክልል ይገነባል ተብሎ የሚጠበቀው የመጀመሪያው የቴክኖሎጂ ከተማ የአገሪቷን ታሪክ መሰረት በማድረግ የሚከናወን መሆኑ ተገለጸ። እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል ተብሎ የሚጠበቀው ና በባህር ዳር ከተማ ዙሪያ በምትገኘው ጢስ አባይ የሚገነባውን የቴክኖሎጂ ከተማ አስመልክቶ የመጀመሪያው አውደ ጥናት ዛሬ ተካሄዷል። በዚሁ ጊዜ እንደተገለፀው ለቴክኖሎጂ ከተማው ግንባታ ባህር ዳር  የተመረጠችው  ከተማዋ የአባይ ወንዝ መገኛና የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ መሰረት በመሆኗ ነው። የቴክኖሎጂ ከተማውን የሚገነባው የአሜሪካው ‘ሀብ ሲቲ ላይቭ ፕሮጀክት' ከሳይንስና ቴክኖሊጂ ሚኒስቴር እና ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ጋር በመተባበር ነው። አውደ ጥናቱ "ኢትዮጵያ እውነተኛዋ ዋካንዳ" በሚል ሀሳብ ነው የተካሄደው። ዋካንዳ በጥር ወር 2010 ዓ.ም በአሜሪካዊው ማርቭል ስቱዲዮ ለእይታ የበቃውና ወንጀልን ለመታገል ቆርጦ በተነሳ የአንዲት ምናባዊ የመካከለኛ አፍሪካ አገር መሪ የስኬት ጉዞ ላይ የሚያጠነጥነው “ብላክ ፓንተር” የተሰኘ ፊልም ውስጥ የተጠቀሰ የቦታ ስም ነው። በፊልሙ ላይ ዋካንዳ በምስራቅ አፍሪካ የምትገኝ የቴክኖሎጂ አገር ስትሆን ይህች ምናባዊ አገር ከቴክኖሎጂ ከተማነቷ ባለፈ የዓለም የስልጣኔ መሰረት ተደርጋ ተገልፃለች። የታሪክ ተመራማሪዎች ፊልሙ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ነው ይላሉ። የሀብ ሲቲ ላይቭ ፕሮጀክት ተባባሪ መስራች ሚካኤል ካሚል ከተማው የሚገነባው የፊልሙ ምናብ የሆነችውን ዋካንዳ መሰረት በማድረግ ቢሆንም የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ ገጽታ በሚያሳይ መልኩ አንደሚከናወን ተናግረዋል። በተለያዩ ሶስት ምእራፎች የሚካሄደው የቴክኖሎጂ ከተማው ግንባታ በመጀመሪያ ምዕራፍ የፈጠራ ጥበብን የሚያሳይ ህንጻ፣ በሁለተኛ ምዕራፍ ፓርኮችንና በሶስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ሆቴሎችና ሌሎች የመዝናኛ ማዕከላት ይገነባሉ ተብሏል። ህንጻዎቹ ጊዜው የደረሰባቸው ቴክኖሎጂዎችን የተላበሰ እንዲሆኑ ይደረጋል። በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ ግንባታ ኢኮኖሚያዊ አዋጪነት ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑን የሀብ ሲቲ ላይቭ ፕሮጀክት ተባባሪ መስራች  አቶ ሚካኤል ገልፀዋል። የኢኮኖሚ አዋጪነት ጥናቱ አንደተጠናቀቀ በመጪው ዓመት ግንባታው  ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት አቶ ሚካኤል ለግንባታውም እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። የቴክኖሎጂ ከተማው ከኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ጋር ተጣጥሞ የሚሰራ እንደሆነም ተናግረዋል። "የጥቁር አሜሪካውያንና አፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት የሆነቸው ኢትዮጵያ በቀጣይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስልጣኔዋን በመጠቀም በቴክኖሎጂ የላቀ ደረጃ የመድረስ አቅም አላት፤ የሚገነባው ከተማም ይህንኑ የሚያመላክት ይሆናል" ብለዋል። በኢትዮጵያ የሚገኙ ጥንታዊ ጽሁፎች ተመራማሪ የሆኑት እጩ ዶክተር መጋቢ ሀዲስ ሮዳስ ታደሰ ኢትዮጵያ በኪነ ህንጻና በከተሞች ግንባታ አስገራሚ ታሪክ እንዳላትና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ግንባታ ዋነኛው ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ቴክኖሎጂ ባልነበረበት ወቅት ኢትዮጵያውያን በአስደናቂ ጥበብ ከተማና ህንጻ ሲገነቡ እንደነበር ገልጸው በስነ ፈለግ(ከዋክብት) ምርምር በማድረግም የመጀመሪያዋ አገር እንደሆነች አንስተዋል። የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ማዕከል ናሳ በንግስት ካሶፒያ ስም የተሰየሙ ኮከቦችን በዓለም የመጀመሪያዎች የኮከቦች ስብሰብ ስያሜ በሚል እውቅና ሰጥቶታል ብለዋል። በባህርዳር የሚገነባው የቴክኖሎጂ ከተማ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን ታሪክ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ በተሻለ መልኩ ማስተዋወቅ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው የቴክኖሊጂ ከተማው ግንባታንና አጠቃላይ ሀሳብ መንግስት የሚደግፈው በመሆኑ ለግንባታው ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል። የቴክኖሎጂ ከተማው ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተጣጣመና የተሳሰረ መሆኑ በሌሎች አገራት ከተገነቡ የቴክኖሎጂ ከተሞች ለየት የሚያደርገው እንደሆነም ጠቅሰዋል። ከተማዋው ለቴክኖሎጂ ዘርፉ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በኢኮኖሚው ላይ በጎ ተጽእኖ እንደሚኖረውም ገልጸዋል። በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ በከተማ የሚኖረው ህዝብ እየጨመረ በመምጣቱ በከተሞች የሚኖሩ ዜጎችን ወቅታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተደገፉ ከተሞች መገንባት አማራጭ የሌለውና ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ እንደሆነም ተናግረዋል። መንግስት ብዛት ያለው ህዝብ በሚኖርባቸው ከተሞች ያለውን በቴክኖሎጂ የበለጸጉ ከተሞችን  የቴክኖሎጂ ከተሞች መገንባትና የገጠር ቀበሌዎችና ወረዳዎችን ወደ ትናንሽ ከተሞች የመቀየር ስራ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ነው ብለዋል። በቀጣይ የባህር ዳር ዙሪያ ከተማ በሆነችው ጢስ አባይ ስለሚገነባው የቴክኖሎጂ ከተማ የምክክር መድረኮች እንደሚዘጋጁም ጠቁመዋል። ለግንባታው የሚያስፈልገው ወጪ በአሜሪካና በተለያዩ አገራት በሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችና ከሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ ምንጮች እንደሚሰበሰብ በምክክር መድረኩ ላይ ተገልጿል። ሀብ ሲቲ ላይቭ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ከሚገነባው የቴክኖሎጂ ከተማ በተጨማሪ በአሜሪካ ካሊፎርኒያና በቻይና ጉዋንዡ ግዛቶች መሰል ከተሞችንም ይገነባል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም