የሀገሪቱን ከተሞች ጽዱ ፣ አረንጓዴና ለመኖሪያ ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው

110

ደብረብርሀን ፤ ጥቅምት 16/2014 (ኢዜአ) የሀገሪቱን ከተሞች ጽዱ ፣አረንጓዴ፣ ውብ እና ለመኖሪያ ምቹ በማድረግ ስነ- ምህዳራቸው የተጠበቀና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እንዲችሉ እየሰራ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

የከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣ አወጋገድ እና በአረንጓዴ ልማት ስራዎች ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ  በደብረብርሀን ከተማ እየተካሄደ ነው።

የሚኒስቴሩ የቤቶችና የከተማ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሄኖስ ወርቁ በመድረኩ እንዳሉት፤  በከተሞች ታሪካዊ  ስፍራዎችን  ንጹህ፣ ውብና ማራኪ በማድረግ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ይገባል።

ሚኒስቴሩ አረንጓዴ  ኢኮኖሚን በመተግበር የሀገራችን ከተሞች ጽዱ ፣አረንጓዴ፣ ውብ እና ለመኖሪያ ምቹ በማድረግ ስርዓተ ምህዳራቸውን የተጠበቀና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እንዲችሉ እየሰራ ነው ብለዋል ።

በዚህም በተባበሩት መንግስታት ልማት ድርጅት እና ግሎባል ኢንቫይሮመንታል ፋስሊቲ በሚደገፍ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በአዳማ ፣ባህርዳር፣  ቢሾፍቱ ፣ድሬደዋና ሀዋሳ  ከተሞች  ፕሮጀክት ተቀርፆ የትግበራ ስራ መጀመሩን  ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ  የደረቅ ቆሻሻ ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት ቀይሮ  የተራቆቱ የከተማ ቦታዎችን በማልማት የአካባቢ በካይ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ የሚሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚሁ ፕሮጀክት ቆሻሻን ለመቀነስና መልሶ ለመጠቀም  የሚያስችሉ  ስድስት  የ”ኮምፖስት” ሼዶች ተገንብተው የተፈጥሮ ማዳበሪያ  ማምረት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም ከ45ሺህ ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የማምረት አቅም መፈጠሩን እና ምርቱንም   ለማሳደግ ተጨማሪ ማሽኖች ተገዝተው እየሰሩ መሆኑን  ተናግረዋል ።

በአረጓዴ ልማቱና ደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ዙሪያ እስካሁን ከ68ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው የተገኙት ውጤቶች አመርቂ መሆናቸውን አብራርተዋል ።

የተገኙ ምርጥ ተሞክሮችን ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋት አሁን ላይ አማካሪ ተቀጥሮ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡ አካባቢውን ከቆሻሻ በመጠበቅ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር መደገፍ እንደሚገባ አመልክተዋል

የደብረብርሀን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ በበኩላቸው፤ የከተማዋን ፈጣን እድገት ተከትሎ የነዋሪዎች ቁጥርም እየጨመረ በመምጣቱ አካባቢውን  ለኑሮ ፣ ለኢቨስትመንትና  ለንግድ ምቹ ለማድረግ  የአረንጓዴ ልማትና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድን የማዘመን ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

ከደረቅ ቆሻሻ  አወጋገድና አረንጓዴ  ልማት  ጋር ተያይዞ ከነዋሪዎች የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶች ለመፍታት ከበዓለም ባንክ በተገኘ 300 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ለመትከል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረኩ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ  ባለድርሻ አካላት  እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም