በኩታ ገጠም ማሳን ማልማት ምርታማነትን እንደሚያሳድግ ተገንዝበናል - የምእራብ ጎንደር አርሶ አደሮች

65
መተማ ነሀሴ 12/2010 በኩታ ገጠም ማሳን ማልማት ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ከቡቃያው አያያዝ መገንዘባቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በምዕራብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ ፡፡ በመተማ ወረዳ የተሻሻለ የግብርና አሰራርን በመጠቀም በኩታ ገጠም እየለማ ያለውን የሰሊጥ ማሳ ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የተወጣጡ አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች ጎብኝተውታል፡፡ በዞኑ ከ8 ሺህ 400 ሄክታር በላይ ኩታ ገጠም መሬት በሰሊጥ ዘር ተሸፍኖ እየለማ መሆኑ ተመልክቷል። በመተማ ወረዳ ለምለም ተራራ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አርሶ አደር  ኢብራሒም ሰይድ በሰጠው አስተያየት ሰሊጥን በኩታ ገጠምና ሙሉ ፓኬጆችን በመጠቀም ማሳውን በመሸፈኑ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቅ ተናግሯል፡፡ “ባለፈው ሰሊጥን በብተናና ምንም አይነት ግብዓት ሳልጠቀም በመዝራቴ ከሁለት ሄክታር መሬት አራት ኩንታል ምርት በማምረት ለኪሳራ ተዳርጊያለሁ” ብለዋል። በዚህ የምርት ዘመን ግን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀምና ከአካበቢው አርሶ አደሮች ጋር በመነጋገር በኩታ ገጠም በሰሊጥ ከሸፈነው  አራት ሄክታር መሬት ከ40 ኩንታል በላይ እንደሚጠብቅ ገልጿል፡፡ ከምዕራብ አርማጭሆ ተሞክሮ ለመቅሰም የመጡት አርሶ አደር ግርማ መብራቱ በበኩላቸው በኩታ ገጠም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም የተሻለ ምርት ሊያስገኝላቸው እንደሚችል መገንዘባቸው ገልፀዋል። ከጉብኝቱ ባገኙት ልምድም በዚህ ዓመት ለጤፍ ያዘጋጁትን ማሳ በመስመር ለመዝራት መወሰናቸውን ተናግረዋል። “በዚህ ዓመት ሰሊጥን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም ባልችልም አሁን ባየሁት ነገር የተማርኩ በመሆኑ በቀጣይ ሙሉ በሙሉ በመስመር ለመዝራት ከወዲሁ እዘጋጃለሁ'' ብለዋል። ከቋራ ወረዳ ለጉብኝት የመጡት አርሶ አደር አለበል ዋሴ በበኩላቸው በኩታ ገጠም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መዝራት በባህላዊ መንገድ ከሚዘራው የበለጠ ምርት እንደሚገኝ እንደተረዱ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘውም በቀጣይ የተሻሻለ የግብርና አሰራርን በመጠቀም ራሳቸውን ለመለወጥ እንደተዘጋጁና ለመጡበት ወረዳና አካባቢ ልምዱን እንደሚያካፍሉ ተናግረዋል፡፡ የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታከለ ሀብቴ እንደገለፁት በሰብል ልማት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ዘመናዊ ቴክኖሎጂንና የግብርና ግብዓቶችን መጠቀም  ግድ ይላል ብለዋል፡፡ ዞኑ ለውጭ ምንዛሬና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ሰብሎች የሚመረቱበት በመሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለመጠቀምና በኩታ ገጠም ለማልማት አቅደው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ “በአቀድነው ልክ ማሳካት ባንችልም በዚህ ዓመት ለቀጣይ ትምህርት የሚሆኑ ስራዎች ተሰርተዋል'' ያሉት አቶ ታከለ ከስምንት ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት የሰሊጥ ሰብል በኩታ ገጠም መልማቱን ጠቁመዋል፡፡ የተፋጠነ ሙሉ ፓኬጅን ተግባራዊ ለማድረግ በዞኑ በሁሉም ቀበሌዎች የሚገኙ አመራሮች ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ194 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በሰሊጥ ዘር የተሸፈነ ሲሆን ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም